አቃቤ ህግ በአቶ ተስፋዬ ኡርጌ ላይ ክስ ሊመሰርት ነው

81
አዲስ አበባ ጥቅምት 12/2011  አቃቤ ህግ በመስቀል አደባባይ በተጠራ የድጋፍ ሰልፍ ላይ የደረሰው የቦምብ ጥቃት ተጠርጣሪ አቶ ተስፋዬ ኡርጌ ላይ ክስ ሊመሰርት ነው። ልደታ በሚገኘው የፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት በተጠርጣሪው ላይ ምርመራ ሲያደርግ የነበረው የመርማሪ ፖሊስ ቡድን መዝገቡን ለአቃቤ ህግ ማስረከቡን ገልጿል። አቃቤ ሕግም ከወንጀሉ ውስብስብነት አኳያ ክስ የመመስረቻ የ15 ቀናት ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል። ተጠርጣሪው አቶ ተስፋዬ ኡርጌ በበኩላቸው አቃቤ ህግ የጠየቀው ጊዜ ረጅም ነው በሚል ተቃውሞታል። ፍርድ ቤቱ የወንጀል ድርጊቱን ክብደትና ውስብስብነት ከግምት ውስጥ በማስገባት የተጠየቀውን የ15 ቀናት የክስ መመስረቻ ጊዜ ፈቅዷል። በዚህም የአቃቤ ሕግን ክስ ለመስማት ለጥቅምት 27 ቀን 2011 ዓ.ም ቀጠሮ ይዟል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ተጠርጣሪው አቶ ተስፋዬ ኡርጌ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የስም ማጥፋትና የተዛባ ዘገባ እንደወጣባቸው በመግለጽ፤ ፍርድ ቤቱ ለተቋማቱ የማስተካከያ ትዕዛዝ እንዲሰጥ ጠይቀዋል። ለአብነትም በቤታቸው የቦምብና ህገ-ወጥ መሳሪያ መገኘቱን መዘገቡን ገልጸው፤ ነገር ግን ከአንድ ህጋዊ ሽጉጥ በስተቀር ምንም አይነት የጦር መሳሪያ በቤታቸው አለመገኘቱን አስረድተዋል። ፍርድ ቤቱ በበኩሉ ተጠርጣሪው በሕጋዊ ማስረጃ የተደገፈ አቤቱታ አለማምጣቸውን በመግለጽ፤ ጥያቄውን ውድቅ አድርጎታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም