ሀገራዊ ለውጡ እንዳይቀለበስ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ የድሬዳዋ የኦነግ አባላትና ደጋፊዎች ተናገሩ

51
ድሬደዋ ጥቀምት 11/2011  የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) በመላ ሀገሪቱ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችን በመክፈትና ከአባላትና ደጋፊዎቹ ጋር በመገናኘት የተገኘውን ሀገራዊ ለውጥ ከዳር ለማድረስ እንደሚሰሩ የግንባሩ ከፍተኛ አመራሮች ተናገሩ። በድሬዳዋ የኦነግ ደጋፊዎችና አባላት ዛሬ ለኦነግ አመራሮች ደማቅ አቀባበል አድርገዋል፤ ሀገራዊ ለውጡ ወደኋላ እንዳይቀለበስ የተመዘገቡ ውጤቶችን ለማጎልበት እንደሚንቀሳቀሱም ገልፀዋል፡፡ ዛሬ በድሬዳዋ በተካሄደው ደማቅ የአቀባበል ሥነ-ሥርዓት ላይ የኦነግ የምስራቅ ሀረርጌ ምክትል ሊቀመንበር አቶ አራርሶ ቢቂላ እንደተናገሩት የኦሮሞ ህዝብ ለነጻነቱ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ባደረገው ተጋድሎና ዲፕሎማሲያዊ ጥረት አሁን ለተገኘው ጅምር ውጤት በቅቷል፡፡ በተለይ ባለፉት አራት ዓመታት ቄሮዎች የከፈሉት መስዋዕትነትና ያፈሰሱት ደም ዛሬ ለተገኘው ድል ትልቅ አበርክቶ እንዳለው አቶ አራርሶ ተናግረዋል፡፡ "ሀገራዊ ለውጡን ወደ ማይቀለበስበት ደረጃ ለማድረስ ግንባሩ ከፊንፊኔ ጀምሮ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ቅርንጫፎችን ከፍቶ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ከአባለቱና ከህዝቡ ጋር ተቀናጅቶ ይሰራል" ብለዋል፡፡ በተለይም የኦሮሞ ህዝብ አንድነቱን ይበልጥ አጠናክሮ ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር በእኩልነት፣ በፍቅርና በአንድነት በመሆን ቀጣዩን ተልዕኮ እንደሚወጣ ጠቁመው ግንባሩ ህግና ሥርዓትን ጠብቆ ከመንቀሳቀስ ባለፈ ከፌደራልና ከኦሮሚያ መንግስት ጋር እንደሚሰራም ገልፀዋል፡፡ እንደ አቶ አራርሶ ገለጻ ወጣቶች በመላው ሀገሪቱ የተገኘውን ለውጥ ለመቀልበስ የሚፈልጉ አካላትን ነቅተው በመጠበቅና አጥፊዎችን ለህግ አሳልፈው በማቅረብ የኦሮሞ ህዝብ በአሁኑ ወቅት ማጣጣም የጀመረውን ነጻነት ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል፡፡ የኦነግ ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ ሮራስ አባ ጎባ በበኩላቸው የኦሮሞ ህዝብ ላለፉት በርካታ ዓመታት የተጫነበትን ቀንበርና ጭቆናን በመቃወም ከሌሎች የሀገሪቱ ህዝቦች ጋር በመሆን ባደረገው ቆራጥ ተጋድሎና በከፈለው መስዋዕትነት ለዛሬው ታላቅ ቀን መብቃቱ ገልጸዋል፡፡ የኦሮሞ ህዝብ በተለይ ወጣቶች አሁን በሀገሪቱ የተገኘውን ለውጥ በሰከነ መንፈስ ማስቀጠልና ዳር ማድረስ እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል፡፡ " የኦሮሞ ህዝብ ከተለያዩ እምነት ተከታዮች፣ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር ያዳበረውን በፍቅርና በህብረት የመኖርን ታሪካዊ እሴቶቹን ጠብቆ ለውጡን ዳር ሊያደርስ ይገባል" ብለዋል፡፡ ኦነግ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚጉ አባላቱንና ደጋፊዎቹን በማስተባበር በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለውን የለውጥ ጉዞ ለማስቀጠል የድርሻውን እንደሚወጣም ጠቁመዋል። የኦነግ አመራሮችን በደማቅ ሥነ ሥርዓት የተቀበሉት የድሬዳዋ አባላትና ደጋፊዎች አመራሮቹ ድሬዳዋ በመገኘታቸው የተሰማቸውን ታላቅ ደስታ ገልፀዋል፡፡ ከግንባሩ ጋር በመሆን የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ ወደ ማይቀለበስበት ደረጃ ለማድረስ ተግተው እንደሚሰሩም ተናግረዋል፡፡ ወጣት ሃምዲያ አሚን "የኦሮሞ ህዝብ አንድነቱን ጠብቆ በመደማመጥና በመተጋገዝ የተገኘውን የነጻነት ጎዳና ዳር ያደርሳል፤ እኔም ኃላፊነቴን በተሻለ ለመወጣት ተዘጋጅቻለሁ" ብላለች፡፡ "ዛሬ ያ ሁሉ መከራ አልፎ፣ ስደትና ሞት ቀርቶ ከምንወደው ድርጅት ጋር መገናኘታችን ያስደስተናል" ያለው ደግሞ ወጣት አህመድ ኑር ኡስማኤል ነው፡፡ "ከሁሉም የሀገሪቱ ህዝቦች ጋር በፍቅርና በአንድነት በመሆን የለውጡን አደናቃፊዎች እንፋለማለን" ሲልም ተናግሯል፡፡ ለተገኘው ሀገራዊ ለውጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፣ አቶ ለማ መገርሳና አጋሮቻቸው ሊመሰገኑ እንደሚገባ የገለጸችው ወጣት ሳሊያ ሰይፈዲን በበኩሏ እነሱ የጀመሩትን ለውጥ ከዳር ለማድረስ ከኦነግ ጋር በመሆን ኃላፊነቷን እንደምትወጣ  ገልጻለች፡፡ "ዛሬ የኦሮሞ ህዝብ ዳግም የተወለደበት የደስታ ቀን ነው" ያሉት ደግሞ አዛውንቱ አቶ መሐመድ ዩሱፍ ናቸው፡፡ " እየታየ ያለው ሀገራዊ ለውጥ ከዳር የሚደርሰው በሀገሪቱ ካሉ ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ጋር በአንድነት የመጓዝ ግዴታችንን ስንወጣ ነው›› ብለዋል፡፡ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፈጅረዲን ሙሳ በበኩላቸው " የኦሮሞ ህዝብ አንድነቱን አጠናክሮ ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ጋር በፍቅር በመኖር ለተሻለ ድልና ለውጥ በጋራ መስራት ይኖርበታል" ብለዋል፡፡ ከኦነግ ጋር በመተጋገዝ ለመስራት ፓርቲያቸው ዝግጁ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም