በህንድ ዴልሂ በተካሄደ ግማሸ ማራቶን ውድድር በሁለቱም ጾታ ኢትዮጵያን አትሌቶች አሸነፉ

79
አዲስ አበባ ጥቅምት 11/2011 በህንድ ዴልሂ በተካሄደ ግማሸ ማራቶን ውድድር በሁለቱም ጾታ ኢትዮጵያን አትሌቶች የበላይነት ወስደው አጠናቀዋል። በሴቶች መካከል የተደረገውን ውድድር አትሌት ፀሀይ ገመቹ የቦታውን ክብረወሰን በመስበር ጭምር አሸናፊ ሆናለች። አትሌት ፀሀይ 1 ሰዓት ከ6 ደቂቃ ከ50 ሴኮንድ በሆነ ሰዓት በመግባት ከዘጠኝ ዓመት በፊት በኬኒያዊቷ ሜሪ ኬታን ተይዞ የነበረውን የቦታውን ክብረ ወሰን በአራት ሴኮንድ ማሻሻል ችላለች። የአሸናፊነት ግምት ተሰጥቷት የነበረችው አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ስድስተኛ ደረጃ በመያዝ ውድድሩን ጨርሳለች። በዚህ ውድድር ኬኒያዊቷ ጆይሲሊን ጄፕካሶጌ ሁለተኛ ስትወጣ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ዘይነባ ይመር ደግሞ ሶስተኛ ሆና ጨርሳለች። በወንዶች መካከል የተደረገውን ውድድር ደግሞ ኢትዮጵያውያኑ አትሌት አንዱአምላክ በልሁ በአንደኛ እንዲሁም አትሌት አምደወርቅ ዋለልኝ ደግሞ ሁለተኛ ሆኖ ውድድሩን በበላይነት አጠናቀዋል። በተያያዘ ዜና በአምስተርዳም በተደረገው የማራቶን ውድድር በሴቶች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘው ሲያጠናቅቁ በወንዶች ደግሞ ሁለተኛና ሶስተኛ ሆነው አጠናቀዋል። በዚህ ውድድር በወንዶች ኬኒያዊው ሎረንስ ቺሮኖ አንደኛ ሆኖ አጠናቋል። ኢትዮጵያውያኑ አትሌት ሙሌ ዋስይሁንና አትሌት ሰለሞን ዲካሳ ሁለተኛና ሶስተኛ ወጥተዋል። በአምስተርዳም የሴቶች የማራቶን ውድድር ደግሞ አትሌት ታደለች በቀለ በአንድኛነት አጠናቃለች። አትሌት ሻሼ ዓለሙ ሁለተኛ፣ አትሌት አዝመራ ገብሩ ሶስተኛ በመሆን ተከታትለው በመግባት ውድድሩን በበላይነት ፈጽመዋል። በአምስተርዳም ማራቶን የተካፈለው ታዋቂው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ የሆድ ህመም ስለተሰማው ውድድሩን አቋርጦ ሊወጣ መገደዱን ገልጿል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም