ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለደመወዝ ጭማሪ የሰጡት ማብራሪያ ወቅታዊና ተገቢ ነው ---የትግራይ ማዕከላዊ ዞን ሠራተኞች

134
አክሱም ጥቅምት 11/2011 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የመንግስት ሠራተኞች የደመወዝ ጭማሪን አስመልክተው የሰጡት ማብራሪያ ወቅታዊና ተገቢ መሆኑን በትግራይ ማዕከላዊ ዞን አስተያየታቸውን የሰጡ የመንግስት ሠራተኞች ገለጹ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥቅምት 6 ቀን 2011 ዓ.ም ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡ በዞኑ የሚገኙ አንዳንድ የመንግስት ሠራተኞች ማብራሪያውን አስመልክተው ለኢዜአ እንደገለጹት ዘንድሮ የደመወዝ ጭማሪ እንደማይኖር በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበው ወሳኔ ቅር የሚያሰኝ ቢሆንም ሀገሪቱ ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ አኳያ ተገቢ ነው። ዘንድሮ የደመውዝ ጭማሪ አለመደረጉ በስራቸው ላይ የሚፈጥረው አሉታዊ ተጽእኖ እንደማይኖርም ሰራተኞቹ ተናግረዋል። በላዕላይ ማይጨው ወረዳ የሲቪል ሰርቪስ መስሪያቤት ሠራተኛ አቶ አማኑኤል ኃይለ  እንዳሉት የአገሪቱን የኢኮኖሚ እድገት መሰረት ያደረገ የደመወዝ  ጭማሪ ጠብቀው እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ይሁንና መንግስት በተለያየ ምክንያት የደመወዝ ጭማሪ እንደማያደርግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹበት አግባብና ያቀረቧቸው ምክንያቶች  ተቀባይነት ያላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ " አገራችን በአሁኑ ወቅት ያጋጠማት የበጀት አጥረትና ያላትን የእዳ ጫና ግምት ውስጥ በማስገባት ክስተቱን  ቅድሚያ ሰጥቶ ለማስተካከል መንግስት  መወኑ ተገቢ ነው" ብለዋል። መንግስት የሀገሪቷን ኢኮኖሚ ፈጥኖ በማረጋጋት የመንግስት ሠራተኞችን ደመወዝና ጥቅማጥቅም የተመለከቱ ጉዳዮችን ለቀጣይ ትኩረት እንዲሰጥበት ጠይቀዋል፡፡ የዞኑ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ሠራተኛ ወይዘሮ ህይወት መለስ በበኩላቸው "ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የደመወዝ ጭማሪን አስመልክቶ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያደረጉት ንግግር ትክክለኛና ተቀባይነት ያለው ነው" ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስት ከደመወዝ ጭማሪ በፊት ቅሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮች እንዳሉና በአሁኑ ወቅት መጨመሩ ሊያስከትለው የሚችለውን ችግር  ያብራሩበት መንገድም ተገቢነት ያለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ "የደመወዝ ጭማሪ ባለመደረጉ የመንግስት ሠራተኛው ሥራውን መበደል አይኖርበትም" ብለዋል። "የኑሮ ውድነት በየጊዜው እየጨመረ በመሆኑ ገበያን የማረጋጋት ሥራ ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል" ሲሉም ነው የገለጹት፡፡ "የደመወዝ ጭማሪ የለም ሲባል እንደ መንግስት ሥራተኛ  ቅር ተሰኝቻለሁ"  ያሉት ደግሞ  ሌላው የዞኑ አስተዳደር ሠራተኛ አቶ ለአከ አባይ  ናቸው፡፡ "ይሁንና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደመወዝ እንዳይጨመር ያቀረቧቸው ምክንያቶች ተገቢና አሳማኝ በመሆናቸው ውሳኔውን ተቀብያለሁ "ብለዋል፡፡ "ቅድሚያ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መረጋጋት ተገቢ ነው" ያሉት አቶ ለአከ አገሪቱ የገጠሟት ችግሮች ለሠራተኛው ደመወዝ እንዳይጨመር የሚያደርጉ አሳማኝ ምክንያቶች መሆናቸውን አረጋግጠዋል። የአክሱም ከተማ አስተዳደር ሠራተኛ ወይዘሮ ለተብርሃን ግደይ በበኩላቸው "የመንግስት ሰራተኛውን ኑሮ ለማሻሻል  የደመወዝ ጭማሪ ማድረግ ብቻ ለውጥ አያመጣም" ብለዋል። "መንግስት ከደመወዝ ጭማሪ ባለፈ ገበያ የማረጋጋትና ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማምጣት መስራት ይጠበቅበታል" ሲሉ ተናግረዋል። እንደ ወይዘሮ ለተብርሀን ገለጻ መንግስት አሁን ካለው ወቅታዊ ሁኔታ ቅድሚያ ኢኮኖሚን ለማረጋጋትና የሀገሪቱን እዳ ለማቅለል ብሎ የወሰደው እርምጃ ተገቢ ነው።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም