በትግራይ መልሰው ያገገሙ ተፋሰሶችን ህብረተሰቡ በባለቤትነት እንዲረከባቸው እየተደረገ ነው---ማህበራዊ ረድኤት ትግራይ

87
መቀሌ ጥቅምት 11/2011 በትግራይ ክልል በአካባቢ ጥበቃ ሥራ መልሰው ያገገሙ ከ13 ሺህ ሄክታር በላይ የተፋሰስ መሬቶችን ህብረተሰቡ በባለቤትነት እንዲረከባቸው እየተደረገ መሆኑን ማህበራዊ ረድኤት ትግራይ አስታወቀ። በክልሉ በሳምረ ሳህርቲና ክልተ አውለአሎ ወረዳዎች በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ ችግሮች ጉዳት ደርሶባቸው የነበሩ ስምንት ተፋሰሶች ወደ ቀድሞ ይዞታቸው እንዲመለሱ መረዱን ማህበሩ ገልጿል። በማህበራዊ ሬድኤት ትግራይ የአካባቢ ጥበቃና ልማት ዳይሬክተር አቶ ደስታ ገብረሚካኤል ለኢዜአ እንደገለጹት ማህበሩ ባለፉት አራት ዓመታት "ድራይ ዴቭ " በሚል መጠሪያ ባቋቋመው ፕሮጀክት በተከናወኑ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች መሬቶቹ መልሰው እንዲያገግሙ ተደርጓል። "በወረዳዎቹ ከ13ሺህ ሄክታር በላይ የተጎዱ ተፋሰሶች መልሰው እንዲያገግሙ ለተከናወኑ የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ከህዝቡ የጉልበት ተሳትፎ በተጨማሪ ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጓል" ብለዋል ። ዳይሬክተሩ እንዳሉት በተፋሰሶቹ ውስጥ የሚገኙ ከ15ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ተደራጅተው  በመስኖ፣ በንብ ማነብና በራስ አገዝ ቁጠባና ብድር አገልግሎቶች ተጠቃሚ ሆነዋል። "በተፋሰሶቹ ውስጥ ደርቀው የነበሩ የውሃ ምንጮች መልሰው በመጨመራቸው አነስተኛ ግድቦች ተገንብተው ከ400 ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ለማልማት መቻሉን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። "አርሶ አደሮች በ25 የቁጠባና ብድር ማህበራት ተደራጅተው ተበድረው የመስራትና የመቆጠብ ባህላቸው እንዲዳብር ተደርጓል " ብለዋል ። እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ መልሰው ያገገሙ ተፋሰሶችን ህብረተሰቡ በባለቤትነት ተረክቦ እንዲጠብቃቸውና እንዲጠቀምባቸው እየተደረገ ነው። የለሙ ተፋሰሶችን በዘላቂት ለማልማትና ለመጠቀም ከህብረተሰቡ ለተውጣጡ የተፋሰስ ልማትና አስተዳደር ኮሚቴዎች ስልጠና የመስጠትና መሬቶችን የመረካከብ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል። " በተፋሰሶቹ በተከናወኑ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች  የአፈር መከላትን በመግታት የመሬት ለምነት እንዲጨምር ተደርጓል" ያሉት ደግሞ የሳምረ ሳህርቲ ወረዳ ግብርናና ገጠር ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብርሀኑ መሀሪ ናቸው፡፡ የተገኘውን መልካም ተሞክሮ በመውሰድ ሌሎች የተጎዱ ተፋሰሶችን ለማልማት የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ኃላፊው አመላክተዋል ። በሳምረ ሳህርቲ ወረዳ የወዛ ተፋሰስ ነዋሪ አርሶ አደር አብረኸት አሰፋ በበኩላቸው የአካባቢ ጥበቃ ስራ ከመሰራቱ በፊት ከእርሻ ማሳቸው ላይ አፈር በጎርፍ እየተወሰደ ይቸገሩ እንደነበር አስታውሰዋል ። አርሶ አደሯ እንዳሉት በአካባቢው የተለያዩ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራዎች በመሰራቱ የማሳቸው ለምነት ተጠብቆ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። "በዘንድሮ ዓመት ማሳዬን ከሁለት ጊዜ በላይ ለማልማት ዝግጅት ላይ ነኝ" ያሉት ደግሞ  ሌላው የተፋሰሱ ነዋሪ አርሶ አደር ኃይለ አብረሀ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም