አኩሪ አተርን በአርሶ አደር ማሳ ላይ የማላመድ ሥራ መጀመሩን የሽሬ ማይጸብሪ ግብርና ምርምር ማዕከል አሳታወቀ

111
ሽሬ እንዳስላሴ  ጥቅምት 11/2011 ወደ ውጭ የሚላኩ የግብርና ምርቶችን ለማሳደግ አኩሪ አተርን በአርሶ አደር ማሳ ላይ የማላመድ ሥራ መጀመሩን በትግራይ ክልል የሽሬ ማይጸብሪ ግብርና ምርምር ማዕከል አስታወቀ፡፡ የማዕከሉ ዋና ዳሬክተር አቶ ዳንኤል ደስታ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ ብዙም ያልተለመደውን  የአኩሪ  አተር ዝርያ ለማላመድ በአርሶ አደሮች ማሳ ላይ ዘሩን የማባዛት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፈላጊ የሆነውን አኩሪ አተር በክልሉ ሰሜናዊ ምዕራብ  ዞን አርሶ አደሮች በስፋት እንዲያመረቱት ጥረት መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ ማዕከሉ ባለፈው ዓመት በሁለት ወረዳዎች  የጀመረውን የማላመድ ሥራ ዘንድሮ ወደ አራት ወረዳዎች ማሳደጉንም ጠቁመዋል፡፡ አቶ ዳንኤል እንዳሉት ባለፈው ዓመት በውስን አርሶ አደሮች በተጀመረው የማላመድ ሥራ ከአንድ ሄክታር መሬት እስከ 30 ኩንታል ምርት በመገኘቱ በአርሶ አደሮች ተቀባይነት እያገኘ መጥቷል፡፡ በተያዘው የምርት ዘመን በ1 ሺህ 223 አርሶ አደሮች ማሳ 600 ሄክታር መሬት የአኩሪ አተር ዝርያ የማላመድና የማባዛት ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ባለፈው ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ በአኩሪ አተር ከሸፈኑት ግማሽ ሄክታር መሬታቸው 13 ኩንታል ምርት ማግኘታቸውን የተናገሩት ደግሞ በዞኑ የታህታይ አድያቦ ወረዳ  ነዋሪ አርሶ አደር በላይ አማረ ናቸው፡፡ ካለፈው ዓመት ተሞክሮ በመውሰድና በባለሙያዎች ድጋፍ ታግዘው በዘንድሮ  የምርት ዘመን አንድ ሄክታር መሬት በአኩሪ አተር ሰብል መሸፈናቸውን ገልጸዋል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ግማሽ ሄክታር ማሳቸውን በእዚሁ ሰብል የሸፈኑት ሌላው የወረዳው ነዋሪ አርሶ አደር መብራህቶም ተክሉ በበኩላቸው የሰብሉ ፍሬ አያያዝ በመልካም ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ አኩሪ አተርን በግብአትነት የሚጠቀሙ ፋብሪካዎች እየተስፋፉ በመምጣታቸው የገበያ ችግር አለመኖሩን የተናገሩት  ደግሞ  የአኩሪ አተር ተመራማሪ አቶ አባዲ ግርማይ ናቸው። ዝርያውን በክልሉ በማለመድ ከሰሊጥ በተጨማሪ አኩሪ አተርን ወደ ውጭ ለመላክ ታሳቢ ያደረ የምርምር ሥራ በማከናወን ላይ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ አኩሪ አተር 40 ከመቶ ፕሮቲን፣ 22 ከመቶ የምግብ ዘይት በውስጡ የያዘና ለሰው ልጅና ለእንስሳት መኖ ጠቃሚ መሆኑን መረጃዎች ዋቢ አድርጎ የዘገበው ኢዜአ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም