በአማራ ክልል በአምስት ወረዳዎች በህገወጦች ተይዞ የነበረ የ72 ሴት አርሶ አደሮች መሬት ተመለሰ

78
ባህር ዳር  ጥቅምት11/2011 በአማራ ክልል በተመረጡ አምስት ወረዳዎች በህገወጦች ተይዞ የነበረ የ72 ሴት አርሶ አደሮች የእርሻ መሬት እንዲመለስ መደረጉን የአማራ ሴቶች ማህበር ገለጸ። መሬቱ ሊመለስ የቻለው ለሙከራ በተተገበረው የሴቶች የአቅም ማጎልበቻ ፕሮጀክት አማካኝነት የሴቶችን አቅም የማጎልበት ሥራ በመሰራቱ መሆኑም ተመልክቷል። ማህበሩ ከኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት ጋር በመተባበር ከአውሮፓ ህብረት ባገኘው ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ  ፕሮጀክቱ በምዕራብ ጎጃም፣ በደቡብና በማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች በሚገኙ አምስት ወረዳዎች ሲተገበር ቆይቷል። በ20 ቀበሌዎች በሚገኙ 4 ሺህ ሴቶች ፕሮጀክቱ ያለው የሁለት ዓመት የትግበራ ቆይታ በባለድርሻ አካላት ትናንት በባህር ዳር ከተማ ሲገመገም የማህበሩ ሊቀመንበር ወይዘሮ አበራሽ ታደሰ እንደገለጹት የገጠር ሴቶችን ሁለንተናዊ አቅም ለማጎልበት የተከናወነው ሥራ ውጤት እያስገኘ ነው። ፕሮጀክቱ በተተገበረባቸው ወረዳዎች በተደረገ የዳሰሳ ጥናት በህገወጦች ተወስዶ ከነበረው የ147 ሴት አርሶ አደሮች የእርሻ መሬት ውስጥ የ72ቱ በድርድርና በፍርድ ውሳኔ እንዲመለስ ለማድረግ መቻሉን ተናግረዋል። በልማት ቡድን ተደራጅተው ስልጠና የወሰዱ ሴቶች በቀጣይ የቀሪዎቹን ሴት አርሶ አደሮች ማሳ ለማስመለስ ጉዳዩን ወደፍርድ ቤት ወስደው በመከታተል ላይ መሆናቸውንም አመልክተዋል። እንደሊቀመንበሯ ገለጻ የችግሩ መንስኤ ለአንድ መሬት ሁለት የመሬት መጠቀሚያ ደብተር መስጠት፣ አድልኦና ብልሹ አሰራር፣ ከባህር መዝገብ መረጃ ውስጥ መሰረዝና የመረጃ አያያዝ ችግሮች ይጠቀሳሉ። ውጤቱ የተገኘው በጾታዊ ትንኮሳ፣ በልጅነት ጋብቻ፣ በመሬት ህጉና በሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ላይ የሚደርሰባቸውን ተጽዕኖ ሴቶች እንዴት መከላከል እንደሚችሉ በቂ ስልጠና እንዲያገኙ በመደረጉ መሆኑንም አስረድተዋል። የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት ዳይሬክተር ወይዘሮ ሳባ ገብረመድህን በበኩላቸው የሴቶችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። "ጥምረቱ ከአውሮፓ ሕብረት ባገኘው የ200 ሺህ ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ በአማራ፣ በጋምቤላና በአዲስ አበባ ለሚገኙ ሴቶች ያከናወነው የአቅም ማጎልበት ሥራ ውጤት እያመጣ ነው" ብለዋል። በቀጣይም የሴቶች አቅም ይበልጥ በስልጠና በማጎልበትና ችግሮችን ነቅሰው በማውጣት መብትና ጥቅማቸውን እንዲያስከብሩ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባም አሳስበዋል። በመድረኩ ላይ የተገኙት የክልሉ ፍትህ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ እሸቴ ተስፋዬ በበኩላቸው "የሴቶችን መብትና ጥቅም ለማረጋገጥ የተጀመረው ቅንጅታዊ አሰራር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት" ብለዋል። "ከመሬት ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮችን ባለድርሻ አካላት እንደየድርሻችን ለይተን በመፍታት የሴቶች መብትና ጥቅም ሳይሸራረፍ እንዲረጋገጥ በትኩረት ልንሰራ ይገባል" ብለዋል። መብታቸው ተጥሶ ሲገኝ ህግን መሰረት ባደረገ አግባብ በማስረጃ ላይ የተመሰረተ የፍርድ ውሳኔ እንዲያገኙ የሚደረግ መሆኑንም አስረድተዋል። "ፕሮጀክቱ የሰጠን የአቅም ግንባታ ስልጠና መብታችንን ለማስጠበቅ  ጉልበት ሆኖናል" ያሉት ደግሞ ከጎንደር ዙሪያ ወረዳ ጺዮን ፀዋጅ ቀበሌ የመጡት ወይዘሮ ነገስ መስፍን ናቸው። አደረጃጀታቸውን በማጠናከርም ከራሳቸው አልፎ የእርሻ መሬታቸው ያለአግባብ የተወሰደባቸውን የሌሎች ሴቶችን መሬት ማስመለስ እንደቻሉም ተናግረዋል። "በሁለት ሳምንት አንድ ጊዜ በምናደርገው የልማት ቡድን ውይይት በእኛ መፍታት ያልቻልነውን የሌሎች አራት ሴት አርሶ አደሮች መሬት የማስመለስ ጉዳይ ለህግ አቅርበን እየተከራከርን እንገኛለን" ሲሉም ገልጸዋል። ከደቡብ ጎንደር ዞን ፋርጣ ወረዳ እንደርጌስ ቀበሌ የሴቶች የልማት ቡድን መሪ ወይዘሮ አማለድ ሺበሽ በበኩላቸው በፕሮጀክቱ ባገኙት ስልጠና ግንዛቤያቸው በማደጉ የተነጠቁትን መሬት ለማስመለስ እንደሚሰሩ ተናግረዋል። በፕሮጀክቱ ያገኙት ስልጠና ከእርሻ መሬት ማስመለስ በተጨማሪ ከሚደርስባቸው ፆታዊ ጥቃትና ከሌሎች ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ራሳቸውን አርቀው ለሌሎች ዘብ እንዲቆሙ ያስቻላቸው መሆኑንም አስረድተዋል። ለአንድ ቀን በተካሄደው የፕሮጀክቱ የሁለት ዓመት አተገባበር ግምገማ ላይም ከክልል፣ ከዞን፣ ከወረዳና ከቀበሌ የተውጣጡ ባለድርሻ አካላትና ሴት አርሶ አደሮች ተሳትፈዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም