ሴቶች የአመራር ብቃታቸውን የሚያሳዩበት ጊዜ አሁን ነው- ተመራማሪዎችና የሴቶች መብት ተሟጋቾች

84
አዲስ አበባ ጥቅምት 11/2011 ሴቶች የአመራር ብቃታቸውን የሚያሳዩበትና አርአያነታቸውን የሚያስመሰክሩበት ጊዜ አሁን መሆኑን ሴት ተመራማሪዎችና የሴቶች መብት ተሟጋቾች ገለጹ። በአገሪቱ ሴቶች በወሳኝ ዘርፎች ላይ የመምራት ዓቅም እንዳላቸው በማህበረሰቡም ሆነ በመንግስት ዘንድ አመኔታ እንዳልነበረና እየተሰጠ የነበረው ተስፋ ከቃል ባለፈ በተግባር ያልተተረጎመ ነበር። በቅርቡ በአገሪቱ በተደረገው የለውጥ ስራ ሴቶች በሚኒስትሮች ካቢኔ አባላት ውስጥ የ50 በመቶ ድርሻ እንዲኖራቸው ተደርጓል። ሴቶች የተሰጣቸውን ዕድል በጥበብ በመጠቀም የአገሪቱን መጻኢ ዕድል የሚወሰንበትን ስራና የአመራር ጥበባቸውን የሚያሳዩበት ጊዜ አሁን መሆኑን የ'ሴቶች ይችላሉ' ማህበር ዳይሬክተር ወይዘሮ የምወድሽ በቀለ ይናገራሉ። ''ከዚህ ቀደም 'ሴቶች እድሉ አልተሰጣቸው ሴቶች አቅም አላቸው' በማለት ነበር መብቶቻቸው እንዲከበሩ የምንሰራው አሁን ግን የተሰጣቸው እድል እንዴት እንደሚጠቀሙ በጋራ በመስራትና ማሳየት አለብን'' ብለዋል። የአገሪቱ ታሪክ ተቀይሮ ሴቶች እንደሚሰሩ በመንግስት የተሰጠውን አመኔታ ወደተግባር በመቀየር ሰላምና ጸጥታ ለማስከበርና የተሻለ ውጤት ለማምጣት መስራት ከሴት ተሿሚዎች የሚጠበቅ ኃላፊነት እንደሆነ ወይዘሮ የምወድሽ ጠቁመዋል።  ሴቶች ለአገር እድገት የተሻለ አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚችሉና ኃላፊነት እንዲሰጣቸው በርካቶች ትግል ያደርጉ እንደነበርም አስታውሰዋል።  ሴት ተመራማሪያን ወይዘሮ መስከረም አዳሙና ወይዘሮ መዓዛ ግርማ እንዳሉት፤ ሴት በምርምር መስክ እንዳትሳተፍና ወደ ከፍተኛ ስልጣን እንዳትመጣ የቤት ውስጥ ጫናዎችና እድሉን ያለማግኘት ሰፊውን ድርሻ  ይይዛሉ። እድሉ ከተሰጣቸው አገርን የሚቀይር ታሪክ እንደሚሰሩ በአለም አደባባይ ማስመስከራቸውን ገልጸዋል። በአገሪቱ ዕድሉን ያገኙ ሴቶች ትውልድን በመቅረጽ ብቃታቸው የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከመፍታትና ሙስናን ከመዋጋት ባለፈ በምርምር ዘርፍ አለምን የሚያስደንቅ ተግባር መፈጸም የሚያስችል አቅም እንዳላቸውም ተናግረዋል። ሴቶች ብልሹ አሰራርን በመታገልና ሙስናን በመጠየፍ ረገድ የተሻለ ስብዕና እንዳላቸው ተናግረው በብዙ ኃላፊነት ተፈትነው ለሚኒስትርነት የበቁት ሴቶች የተጣለባቸውን አደራ በብቃት እንደሚወጡ እምነታቸውን የገለጹት ወይዘሮ መስከረም አዳሙ ናቸው፡፡ ወይዘሮ መዓዛ ግርማ በበኩላቸው  ሴቶች ከተሰጣቸው የስራ ሃላፊነት በተጨማሪ ሌሎች ሴቶችን የማብቃትም ግዴታ ይኖርባቸዋል ፡፡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ አመት፣ 4ኛ የስራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለሹመት ካቀረቧቸው የካቢኔ አባላት መካከል 50 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች እንደነበሩ ይታወሳል።                        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም