ልዩነትን በማስተናገድ ለሰላማዊ መማር ማስተማር የበኩላችንን እንወጣለን -የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች

97
ጥቅምት 11/2011 በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ያሉ ልዩነቶችን በማስተናገድና  በመቻቻል ለሰላማዊ መማር ማስተማር የበኩላቸውን እንደሚወጡ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተናገሩ፡፡ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምን ተማሪዎች ለእውቀትና ለበጎ ነገር እንዲያውሉም መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሲሳይ አበራ እንደተናገረው ዩኒቨርሲቲ ከተለያየ ክልል የተለያዩ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች አብረው የሚኖሩበት በመሆኑ መቻቻልንና አብሮነትን የምንማርበት ቦታ ነው፡፡ “ሰላማዊ የመማር ማስተማር እንዲኖር ከጓደኞቼ ጋር እሰራለሁ” ያለው ተማሪው በተለይ የሃሰት መረጃዎችን ባለመቀባበልና ባለመጋራት የበኩሉን እንደሚወጣ ነው የገለፀው፡፡ ስድስት ኪሎ አካባቢ ያገኘናቸው ወንድማማች  የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሰለሞንና ዋቆ ወደሚማሩባቸው  ዩኒቨርሲቲዎች ሲሄዱ ለሰላማዊ የመማር ማስተማር  የበኩላቸውን እንደሚወጡ  ነው የተናገሩት፡፡ የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የህግ ተማሪው ሰለሞን ወዳጆ እንደገለፀው መማር የባህሪ ለውጥ ማምጣት  ነው፤ህብረተሰብን በሚዛናዊነት ማገልገልም ከተማረው ሃይል ይጠበቃል፡፡ ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን የሚያጠናክሩበት ወሳኝ ጊዜ በመሆኑ በተለይ ለአዳዲስ ተማሪዎች ኢትየጵያዊነትን እንዲገነዘቡ የዩኒቨርሲቲ አስተዳደሮች ሊሰሩ ይገባልም ብሏል፡፡ “በሃገራችን አንዱ ችግር እየፈጠረ ያለው የፍትህ ስርአቱ ነው “ ያለው ተማሪው ህብረተሰቡን ማገልገል ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ሆኖ በዩኒቨርሲቲውም የህግ ተማሪዎች ካውንስል አባል ሆኖ በመስራት የዲሲፕሊን ግድፈት ያለባቸውን ተማሪዎች  የሚመከሩበትን ሁኔታ በማመቻቸት ለሰላማዊ የመማር ማተማር እንደሚሰራም ገልጿል፡፡ “ማህበራዊ ሚዲያ ለጥሩ ነገር ከዋለ ሃገርን እንደሚገነባ ሁሉ፣ሃሰትና የሚያደናግር መረጃ ሃገርን እንደሚያጠፋ በተግባር እያየነው ነው” ያለው ሰለሞን  አብዛኛው የዩኒቨርሲቲ ተማሪ የኢንትርኔት ተጠቃሚ በመሆኑም ትክክለኛ ገፆችን የመጠቀም ልምድን ሊያዳብር ይገባል ብሏል፡፡ የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የመካኒካል ኢንጂነሪንግ ተማሪ ዋቆ ወዳጆ  “ዩኒቨርሲቲ  እንደ ትንሸዋ ኢትዮጵያ የሚቆጠር ነው ፤ይህም ማህበራዊ ህይወትን በማጠናከር ፍቅርና መቻቻልን የተማረበት” እንደሆነ ነው የገለፀው፡፡ መቻቻልና ሰላማዊ የመማር ማስተማርን ለማስፈን ከጓደኞቹ ጋር በመሆን  እንደሚሰራም ነው ተማሪ ዋቆ የተናገረው፡፡ ማህበራዊ ሚዲያ መረጃ ማግኛ  ቢሆንም  እውነታ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ማረጋገጥና የተሳሳተ መረጃን በስሜታዊነት ከማጋራት መቆጠብ ያስፈልጋልም ብሏል፡፡ ህብረተሰቡ ከተማረ ሰው ብዙ ይጠብቃልያለው ተማሪው ሃገር የምትቀየረውም በተማረ ሃይሏ በመሆኑ ይህን ሃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን  ነው  የገለፀው፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም