አንጋፋው የኦሮምኛ ባህላዊ ሙዚቀኛ ለገሰ አብዲ አረፉ

129
አዲስ አበባ ጥቅምት 11/2011 አንጋፋው የኦሮምኛ ባህላዊ ሙዚቃ ተጫዋች ድምጻዊ ለገሰ አብዲ አረፉ። በቀድሞው የሰላሌ አውራጃ ልዩ ስሙ ያያ ቄጤማ የተወለዱት አጋፋው ድምጻዊና የማሲንቆ ተጫዋች ለገሰ አብዲ በኦሮሚኛ ባሕላዊ ሙዚቃ አምባሳደር፣ የመጀመሪያው የማሲንቆ ተጫዋች፣ የግጥምና ዜማ ደራሲ እንደሆኑ ይነገራል። በልጅነታቸው ጀምሮ በተለያዩ የሰርግ ስነ ስርአቶችና ማህበር ላይ በመገኘት ያዜሙ እንደነበር የሚነገርላቸው ለገሰ አብዲ፣ በታዋቂው የኦሮምኛ ዜማ ተጫዋች አቶ ወሰኑ ዲዲ አማካኝነት ወደ አዲስ አበባ መጥተው ክብር ዘበኛ በወታደነት በመቀጠር ስራ ጀምረዋል። በ17 ዓመታቸው ክቡር ዘበኛን የተቀላቀሉት አንጋፋው ሙዚቀኛ በአገር ፍቅር ቴያትር፣ በብሔራዊ ቴያትር፣ በማዘጋጃ ቤት ቴያትር እንዲሁም እንደ ሀብተሚካኤል ደምሴ አይነት የባህል ሙዚቀኞች ጋር በመሆን በተለያዩ የምሽት ክለቦች ሰርተዋል። "ማሲንቆን እንደ ሰው ማነጋገር ይችላሉ" የሚባልላቸው አንጋፋው የጥበብ ሰው በሙዚቃ ሕይወታቸውም አስር ስራዎችን አሳትመዋል፤ በስራዎቻቸው በርካታ ሽልማቶችም ተቀብለዋል። ባጋጠማቸው የጤና ችግር ከስድስት ዓመታት በላይ ማሲንቋቸን ሰቅለው፣ አልጋ ላይ የነበሩት አቶ ለገሰ፣ ትናንት ማምሻውን ማረፋቸው ተሰምቷል። ማሲንቆ በኦሮሚኛ ሙዚቃ ውስጥ ያለውን ጣዕም ያስተዋወቁ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ድምጻዊ ለገሰ አብዲ፤ የሶስት ሴቶችና የ4 ወንዶች ልጆች አባት ነበሩ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም