ተለዋጭ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ባለመዘጋጀቱ ተቸግረናል ... በምዕራብ ሸዋ ዞን ነዋሪዎች

56
አምቦ ጥቅምት 11/2011 በምዕራብ ሸዋ ዞን ከጊንጪ ከተማ ወደ ግንደበረት የሚወስደው መንገድ በአስፋልት ኮንክሪት ለመቀየር ሥራው ቢጀመርም ተለዋጭ የመኪና መንገድ ባለመዘጋጀቱ መቸገራቸውን የአካባቢው ነዋሪዎችና አሽከርካሪዎች ገለጹ፡፡ የአሽከርካሪዎችና የነዋሪዎች ቅሬታ ተገቢ መሆኑን የገለጸው የዞኑ መንገዶች ባለስልጣን በበኩሉ ችግሩን ለመፍታት መንገዱ እየተሰራ ባለበት አካባቢ ተለዋጭ መንገድ እየተዘጋጀ መሆኑን አስታውቋል፡፡ የቅጥቅጥ አይሱዙ መኪና አሽርካሪ የሆነው አዱኛ ኢቲቻ እንዳለው የመንገዱ ግንባታ በተጀመረበት ወቅት ተለዋጭ መንገድ ባለመዘጋጀቱና ዋናው መንገድም በመቆፋፈሩ ቀኑን ሙሉ በመንገድ ላይ ለመዋል ተገደዋል፡፡ "ከግንደበረት ወደ ጊንጪ ለመሄድ ከዚህ ቀደም ሁለት ሰዓት ብቻ የሚወስድው መንገድ በአሁኑ ወቅት ከስምንት ሰዓት በላይ እያስኬደን ነው" ብሏል፡፡ የሚመለከተው አካልም በፍጥነት ተለዋጭ መንገድ በማዘጋጀት የአሽከርካሪዎችና የህብረተሰቡን ችግር መፍታት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ሌላው ቅሬታ አቅራቢ አቶ ጉደታ ንጉሴ በበኩላቸው ከጀልዱ ወረዳ የታመመ ሰው ይዘው ወደ ጊንጪ ለመሄድ ቢነሱም በመንገዱ መቆፋፈር ምክንያት ተሸከርካሪው ማለፊያ በማጣቱ መንገድ ላይ ለማደር መገደዳቸውን ገልጸዋል፡፡ ከእዚህ በተጨማሪ የመንገዱ መበላሸት  30 ብር ያስከፍል የነበረው የትራንስፖርት ታሪፍም በመንገዱ መቆፋፈር  140 ብር ለመክፈል መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡ " በጊንጪ ፍርድ ቤት ጠዋት 4 ሰዓት ላይ ያለኝን ቀጠሮ ለመከታተል ማለዳ 12 ሰዓት ከጀልዱ ብነሳም በመንገድ ብልሽት ምክንያት በቀጠሮ ሰዓት ሳልደርስ በመቅረቴ መዝገቤ ሊዘጋብኝ ችሏል" ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ደንበሊቱ ሂንሰርሙ ናቸው፡፡ መንገዱን ወደአስፋልት ለማሳደግ ሥራዎች ቢጀመሩም ተለዋጭ መንገድ በማዘጋጀት የሕብረተሰቡን እንግልት ማስቀረት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ የምዕራብ ሸዋ ዞን መንገዶች ባለስልጣን ኃላፊ አቶ ቀነኒሳ አብዲሳ ስለ ሁኔታው ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ የአሽርካሪዎችና የነዋሪዎች ቅሬታ ተገቢ መሆኑን ነው የገለጹት። " ችግሩን ለመፍታት መንገዱ በተቆፋፈረበት አካባቢ ተለዋጭ መንገድ እየተዘጋጀ ይገኛል" ብለዋል፡፡ መንገዱን በአስፓልት ኮንክሪት እየሰራ የሚገኘው ኮንትራክተር መንገዱን ለመስራት በቆፈረበት ወቅት የጣለው ከባድ ዝናብ ለችግሩ ሌላው ምክንያት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ መንግስት ህብረተሰቡ ለረጅም ጊዜ ሲያነሳው የነበረውን ጥያቄ ለመመለስ ደረጃውን የጠበቀ የአስፓልት ኮንክሪት መንገድ እየሰራ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፣ በአሁኑ ወቅት እየተስተዋለ ያለውን የትራንስፖርት መጉላላትንም በአጭረ ጊዜ ውስጥ እናስቀራለን ብለዋል፡፡ ከጊንጪ ግንደበረት እየተሰራ ያለው መንገድ 59 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን የህዝቡን ጥያቄ በዘላቂነት ለመፍታት መንገዱን ወደአስፋል ኮንክሪት የማሳደግ ሥራ እየተሰራ ነው፡፡                                  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም