ዩኒቨርሲቲው ሰላማዊ የመማር ማስተማር እንዲሰፍን ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በትብብር እየሰራሁ ነው አለ

58
ደብረ ማርቆስ  ጥቅምት 10/2011 የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የ2011 የትምህርት ዘመን ሰላማዊ የመማር ማስተማር እንዲሰፍን ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ አስታወቁ። ዩኒቨርሲቲው በሰላማዊ የመማር ማስተማር ተግባር  ላይ ከዩኒቨርሲቲውና ከማህበረሰቡ ጋር ተወያይቷል። ፕሬዚዳንቱ ዶክተር ታፈረ መላኩ በውይይቱ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው የትምህርት ዘመኑ ሰላማዊና ጤናማ የሆነ የመማር ማስተማር እንዲኖር  ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት ላይ ይገኛል። በተማሪዎች መካከል ግጭት የሚያስነሱ ችግሮችን ቀድሞ በመለየት ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዳይደናቀፍ እንደሚሰራም አስረድተዋል።በዚህም ተማሪዎች በቆይታቸው ዕውቀት ጨብጠው እንዲወጡ ጥረት እንደሚደረግ አስታውቀዋል። በተለይም የምግብ ጥራት መጓደል፣ የውሃና የኤሌክትሪክ መቆራረጥ፣ መምህራን በቤተመጻህፍት የሌሉ መጻህፍትን ለማጣቀሻነት መስጠትና የመሰሉ ክፍተቶችን ለማቃለል ትኩረት መሰጠቱን ፕሬዚዳንቱ አመልክተዋል። በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ የኮሚኒቲንግ ፖሊስ እንደሚቋቋምና ተማሪዎች አገልግሎት በሚጠይቁበት ጊዜ አፋጣኝ መልስ እንዲሰጥ ይደረጋል ብለዋል። ዩኒቨርስቲው የሚያደርገውን ጥረት የአካባቢው የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና  ሌሎች  አካል ተማሪዎች ወጣ ያለ ባህሪ በሚያሳዩበት ጊዜ እንደራሳቸው ልጆች በማየት መምከርና መገሰጽ እንደሚጠበቅባቸውም ጠቁመዋል። የምሥራቅ ጎጃም ዞን አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አለኽን እንዳሳሰቡት ተማሪዎችና የከተማው ማህበረሰብ ተሸጋጋሪ የሆነ  የሰላምና የፍቅር ግንኙነት ሊኖራቸው ይገባል። የዩኒቨርሲቲውም ሆነ የከተማው ማህበረሰብ እያንዳንዱ ተማሪ ከራሱ ቤት የወጣ አድርጎ መመልከትና አስፈላጊ በሚሆንበት ወቅት ሁሉ እርዳታ ትብብር እንዲያደርግለት አሳስበዋል። የመቶአለቃ ጌታቸው አያሌው በሰጡት አስተያየት ዩኒቨርሲቲ አገር ተረካቢ ዜጎች የሚገነቡበት ተቋም በመሆኑ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራው  ስኬታማ እንዲሆን ድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል። ዩኒቨርሲቲውም ለግጭት ምክንያት የሚሆኑ ችግሮችን ፈጥኖ በመለየት መፍትሄ መስጠትና የተማሪዎች የእርስ በእርስ ግንኙነት ለማጠናከር ትኩረት እንዲሰጥም  ጠቁመዋል። አቶ ታከለ ይስማው የተባሉ አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው እንደአገር ሽማግሌነታቸው አስፈላጊውን ሁሉ በማድረግ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ተግባር ያለ ምንም ችግር በዩኒቨርሲቲው እንዲካሄድ እገዛ ያደርጋሉ።ከሌሎች አካባቢዎች የሚመጡ ተማሪዎችች የመጡበትን ዓላማ አሳክተው እንዲሄዱ እረዳለሁ ብለዋል። ዩኑቨርሲቲው ተማሪዎች ሲያነሱት የነበረው የምግብ ጥራትም ሆነ አቅርቦት ችግሮቹ መስተካከል እንዳለበት አሳስበዋል። በውይይቱ ከሃይማኖት አባቶችና ከአገር ሽማግሌዎች በተጨማሪ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላትና የከተማው ወጣቶችን ጨምሮ 400 ሰዎች ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም