በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመማር ማስተማሩን ሂደት ሰላማዊ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቷል- ርዕሰ መስተዳድር ሚሊዮን

78
ሃዋሳ ጥቅምት 10/2011በደቡብ ክልል በሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የ2011 የትምሀርት ዘመን የመማር ማስተማር ሂደት ሰላማዊ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ገለጹ፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ሚሊዮን ማቲዮስ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት የክልሉ መንግሥት በክልሉ በሚገኙ አሥሩም ዩኒቨርሲቲዎች የመማር ማስተማር ሂደቱን  ያለምንም የጸጥታ ችግር ለማድረግ  በትኩረት እየሰራ ነው፡፡ በአዲሱ የትምህርት ዘመን ሰላማዊ የመማር ማስተማር እንቅስቃሴ እንዲኖር ለማድረግ ሲሰራ እንደነበር የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ የዓመቱ የትምህርት ጊዜ በተያዘለት ጊዜ እንዲጀምር ለማድረግ  ወላጆች ያለምንም ስጋት ልጆቻችውን እንዲልኩ አሳስበዋል፡፡ ትምህርት በጊዜ የተገደበ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የዓመቱ የትምህርት ሥራ ሳይስተጓጎል እንዲሰጥ ነባርም ሆነ አዲስ ተማሪዎች በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ወደ ዩኒቨርሲቲ እንዲገቡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ሥራው ሰላማዊና ውጤታማ እንዲሆን ከሁሉም ከተማ አስተዳደሮች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎቹ በሚገኙባቸው አካባቢዎች ከዞን እስከ ወረዳ ባሉ መዋቅሮች አመራሩ የትምህርት ስራውን ሰላማዊ ማድረግ እንዲቻል እገዛ ያድርጋል ብለዋል። ከኃይማኖት አባቶች፣ከአገር ሽማግሌዎችና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት መደረጉንም ገልጸዋል፡፡ ተማሪዎቹ ወደ ተመደቡባቸው ዩኒቨርሲቲዎች በሚንቀሳቀሱበት ወቀት የትራንስፖርትም ሆነ ሌሎች ችግሮች እንዳይከሰቱ በቅርበት በመከታተል ማስተካከያዎች እንደሚደረጉ ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ በትምህርት ዘመኑ በክልሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተመደቡ አዲስና ነባር ተማሪዎች እንኳን ለአዲሱ የትምህርት ዘመን አደረሳችሁ ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም