መቀሌ 20ኛው አገር አቀፍ የጤና ልማት ጉባዔ ታስተናግዳለች - ኢዜአ አማርኛ
መቀሌ 20ኛው አገር አቀፍ የጤና ልማት ጉባዔ ታስተናግዳለች
76
መቀሌ ጥቅምት 10/2011 ''ጠንካራ የጤና ስርዓት በመገንባት ሁለገብ የጤና ሽፋን ተደራሽነት እናረጋግጥ!'' በሚል መሪ ቃል 20ኛው አገር አቀፍ የጤና ልማት ጉባዔ በመቀሌ ይካሄዳል፡፡ ጉባዔው ከጥቅምት 13 -16/2011 በከተማው የሰማዕታት ሀውልት አዳራሽ ይስተናገዳል፡፡ የትግራይ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ የህዝብ ግኑኝነት ዳይሬክተር አቶ ሙሉጌታ ተስፋይ እንደገለጹት ክልሉ ለ20ኛው አመታዊ የጤና ዘርፍ ጉባዔው ለማስተናገድ ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡ ጉባዔው በመከላከል ላይ ያተኮረውን የጤና ፖሊሲ አፈፃፀም በመገምገም ቀጣይ አቅጣጫዎች ያስቀምጣል ብለዋል፡፡ የእናቶችና ህፃናት እንክብካቤ፣የጤና መድህን ሽፋንና አገልግሎት፣የባለሙያዎች ርህራሄ፣ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ውይይት ከሚደረግባቸው አጀንዳዎች መካከል ናቸው። በክልሎች መካከል ያለውን ግንኙነትና የዕቅድ አፈፃፀም በመገምገም ልምድ መለዋወጫ መድረክ እንደሚሆንም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡ የጉባዔው ተሳታፊዎች በሁለንተናዊ የጤና እንቅስቃሴያቸው አርአያ የሆኑ ወረዳዎችን ይጎበኛሉ፡፡ በተለይም በአገር አቀፍ ደረጃ ዲጂታል የጤና መድህን በተጀመረበት የክልተ አውለአሎ ወረዳን በመጎብኘት ልምድ ያገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም አቶ ሙሉጌታ ተናግረዋል፡፡