በባሌ ዞን የወባ በሽታን ለመከላከል የሚያስችል ስራ እየተከናወነ ነው

134
ጎባ ጥቅምት 10/2011 የክረምቱን መውጣት ተከትሎ ሊከሰት የሚችለውን የወባ በሽታ ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየተሰራ መሆኑን የባሌ ዞን ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡ የጽህፈት ቤቱ የወባና ተላላፊ በሽታዎች መከላከል የስራ ሂደት ባለቤት አቶ አብዱረህማን አብዱ ለኢዜአ እንደገለጹት በዞኑ የክረምቱን መውጣት ተከትሎ ሊከሰት የሚችለውን የወባ ወረርሽኝ ለመቆጣጠር በ15 ወረዳዎች ውስጥ የኬሚካል ርጭት እየተካሄደ ነው፡፡ የኬሚካል ርጭቱ ለወባ በሽታ ተጋላጭ ናቸው ተብሎ በተለዩት ከ120 ሺህ በሚበልጡ መኖሪያ ቤቶች ላይ ከመስከረም መጀመሪያ ጀምሮ እየተካሄደ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ እየተካሄደ ያለው የኬሚካል ርጭትም ከ450 ሺህ ሕዝብ በላይ ከበሽታው መጠበቅ እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ለወባ ትንኝ መራባት ምቹ የሆኑና ውሃ ያቆሩ ረግረጋማ አካባቢዎችን ህብረተሰቡን ባሳተፈ መንገድ የማፋሰስና የማዳረቅ ስራ በመካሄድ ላይ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ በፊት ለወባ በሽታ ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሰራጩት ከ400 ሺህ የሚበልጡ በኬሚካል የተነከሩ የአልጋ አጎበሮችም በአግባቡ ጥቅም ላይ በመዋላቸው በሽታውን ለመከላከል ጉልህ ድርሻ ማበርከታቸውንም አቶ አብዱረህመን ጠቁመዋል፡፡ በዞኑ በወባ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች ላይ በኬሚካል ርጭትና ህብረተሰቡን በማሳተፍ በተሰራው የቅድመ መከላከል ሥራ የበሽታው ስርጭት እየቀነሰ መምጣቱን ከዞኑ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ በወረዳው  የደደቸ በልዓ ቀበሌ ነዋሪው አርብቶ አደር ሁሴን ከማል በሰጡት አስተያየት አካባቢያቸው ወባማ በመሆኑ ከአምስት ዓመታት በፊት በበሽታው ሲሰቃዩ ኖረዋል። በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት አካላት ወባን ለማጥፋት በየዓመቱ ክረምት በሚያካሂዱት ህብረተሰቡን ያሳተፈ እንቅስቃሴ እሳቸውና ቤተሰባቸው በበሽታው ተይዘው እንደማያውቁ ተናግረዋል። ለወባ መራቢያ የሚሆኑ ቦታዎችን ከማጽዳትና ከማፋሰስ በተጓዳኝ የወባ መከላከያ አጎበርን በመጠቀም ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ከበሽታው ለመከላከል መቻለቸውን የተናገሩት ደግሞ በወረዳው የዶቡ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ከሪማ አህመድ ናቸው፡፡ በተለይ የሴቶች የጤና ልማት ሰራዊት በአካባቢያቸው ተደራጅቶ መስራት ከጀመሩ ወዲህ የወባ በሽታ በቀበሌያቸው በወረርሽኝ መልክ ተከስቶ እንደማያውቅ ተናግረዋል፡፡ ሌላው የዚሁ ቀበሌ አርብቶ አደር ሙሳ ወልይ በበኩላቸው ባለፉት ስድስት ዓመታት በአካባቢያቸው በተመደቡ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች እገዛና በህብረተሰቡ ተሳትፎ በሚካሄድ የአካባቢ ቁጥጥር ስራ ከወባ በሽታ ወረርሽኝ ስጋት ነፃ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም