ሚኒስቴሩ የሰላም እሴትን ለማስረፅና አገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል ያስችላል

48
ድሬዳዋ ጥቅምት 10/2011 የሰላም እሴትን ለማስረፅና የተጀመረውን አገራዊ  ለውጡን ለማስቀጠል የሰላም ሚኒስቴር ማቋቋሙ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ አመራሮች ገለጹ፡፡ አመራሮቹ  በድሬዳዋ ከተማ ''ጊዜያዊ ግጭትን በመፍታት ዘላቂ ሰላምና አብሮነት ለማጠናከር የኃይማኖት መሪዎችና የኅብረተሰብ ሚና'' በሚል ርዕስ በተካሄደው ስልጠና ላይ እንደተናገሩት ሚኒስቴሩ በአገሪቱ ሰላምን ለማምጣት ከፍተኛ ድርሻ ይጫወታል ብለው ይጠብቃሉ። በኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የክልል ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ መጋቢ ይታገሱ ኃይለ ሚካኤል እንደተናገሩት፤ በአገሪቱ የሚገኙ ኃይማኖቶች በጋራ የሚጋሯቸውና ለትውልድ እያስተማሩ የሚገኙት ፍቅር፣ ሰላም፣ አንድነት፤ ፍትህና ይቅርታ ማድረግን ነው፡፡ ሚኒስቴሩ ለአገር ወሳኝ የሆኑትን እሴቶች በተለይ በወጣቶችና በሴቶች ውስጥ ለማስረፅ የሚከነወኑትን ተግባራት ውጤታማ ለማድረግ   እንደሚያስችል እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡ ጉባኤው ባለፉት ሰባት ዓመታት የሰላምና የሞራል እሴቶች ግንባታን ለማጠናከርና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የተቋቋመው ተቋም ወሳኝ ሚና እንዳለው የተናገሩት  ደግሞ የጉባዔው  የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ መስዑድ አደም ናቸው፡፡ የድሬዳዋ የኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ቦርድ ፀሐፊ ወንድም ፍሬዘር ጉዴ በበኩላቸው ሚኒስቴሩ በመቋቋሙ የኃይማኖት ተቋማት መደሰታቸውን ይገልጻሉ አገሪቱን ለመገንባት፣ አንድነቷን ለማጠናከርና ሁለንተናዊ ለውጡን ለማስቀጠል ለሰላም እሴት ግንባታ ልዩ ትኩረት መስጠቱ ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ''የሰላም ሚኒስቴር በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች አደረጃጀቱን በመዘርጋት፣ በሰላም እሴት ግንባታ ከኃይማኖት ተቋማት ጋር በመቀናጀት መሥራት ይገባዋል፤  የጀመርነው ሥራ ይበልጥ ውጤታማ ይሆናል'' ብለዋል፡፡ የድሬዳዋ የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፀሐፊ ኡስታዝ ኢዮብ ሐሰን በአገሪቱ የሚወጡ ዕቅዶችና የተጀመሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶች በተቀናጀና በተባበረ መንገድ የሚተገበሩበት አስተማማኝ  ሰላም ሲኖር መሆኑን ገልጸው፣ለዚህም ሚኒስቴሩ ወሳኝ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ባዋቀረው ካቢኔ ውስጥ የሰላም ሚኒሰቴርን አንዱ የሥራ አስፈጻሚ አካሉ አድርጎ ማካተቱ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም