የፍኖተ ሰላም ከተማን የመሰረተ ልማት ችግር ለመፍታት እየተሰራ ነው

67
ባህር ዳር ጥቅምት 10/2011 የፍኖተ ሰላም ከተማ አስተዳደር የከተማዋን የመሰረተ ልማት ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ 61 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ በጀት መድቦ ወደስራ ለመግባት የሚያስችል ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገለጸ። የአስተዳደሩ ከተማ ልማት ቤቶችና ኮንስትራክሽን አገልግሎት ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ያረጋል አይችሉህም ለኢዜአ እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ ከሚከናወኑ የመሰረተ ልማት ስራዎች መካከል የ13 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር የኮብል ድንጋይና የጠጠር መንገድና የውሃ ማፋሰሻ ቦይ ግንባታ ይገኙበታል። እንዲሁም በከተማዋ ሶስት አካባቢዎች አዲስ ለተገነቡ የመኖሪያ መንደሮች የመብራት መስመር ዝርጋታና የአምስት ሸዶች ግንባታ እንደሚከናወን ገልፀዋል፡፡ የመሰረተ ልማት ስራዎቹን ግንባታ ለመጀመርም በአሁኑ ወቅት የዲዛይን ስራዎችን የመስራትና የሚገነቡ መንገዶችን ከሶስተኛ ወገን ነፃ የማድረግ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም አስረድተዋል። እንዲሁም የመሰረተ ልማት ስራዎችን የሚገነቡ ኢንተርፕራይዞችን የመለየት ስራ እየተከናወነ ነው፡፡ በልማት ስራው አንድ ሺህ 900 ለሚጠጉ ሰዎች የስራ ዕድል እንደሚፈጠር ጠቁመዋል። ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ እየተከናወኑ በሚገኙ የመሰረተ ልማት ስራዎች የከተማዋ ገፅታ እየተቀየረ መምጣቱን የተናገሩት ደግሞ የከተማዋ ነዋሪ አቶ ጥላሁን ደሳለኝ ናቸው። ቀደም ሲል የውስጥ ለውስጥና መጋቢ መንገዶች በበጋ ወቅት አቧራ፣ በክረምት ደግሞ ጭቃና ጎርፍ ያስቸግራቸው የነበረ ቢሆንም አሁን መንገዶች በኮብል ድንጋፍ በመገንባታቸው ችግራቸው እየተቀረፈ መሆኑን አስረድተዋል። ሌላኛዋ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ እንኳየ መንግስቱ በበኩላቸው ከኮብል ድንጋፍ ማንጠፍ ስራ ጎን ለጎን የሚገነቡ የውሃ ማፋሰሻ ቦይ ስራዎች በፊት ይገጥማቸው የነበረን የጎርፍ ችግር እንዳስቀረላቸው ተናግረዋል። በቀጣይም አስተዳደሩ የከተማዋን ዕድገት በዘላቂነት ለማፋጠንና ገፅታዋን ይበልጥ ለመቀየር ነዋሪውን በማሳተፍ የጀመረውን የልማት ስራ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ነዋሪዎቹ አሳስበዋል። ጽህፈት ቤቱ ባለፈው ዓመት የከተማዋን መሰረተ ልማት ለማስፋፋት ባከናወነው የልማት ስራ 25 ኪሎ ሜትር የመንገድ ከፈታ፣ ግንባታና ሌሎች የልማት ስራዎች ማከናወኑ ታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም