ኢንሲቲትዩቱ ለውጡን ለማስቀጠል በትኩረት እየሠራ ነው

76
አሶሳ ጥቅምት 10/2011 የኢትዮጵያ ካይዘን ኢስቲትዩት የተጀመረውን  አገራዊ ለውጥ በካይዘን ፍልስፍና እንዲደገፍ ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ፡፡ በካይዘን ፍልስፍና ላይ የተዘጋጀ የልምድ ልውውጥ መድረክ ትናንት በአሶሳ  ከተማ ተካሄዷል፡፡ የኢትዮጵያ ካይዘን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን ያየ ለኢዜአ እንዳስታወቁት  የካይዘን ፍልስፍና ስራን ከብክነት በጸዳ መልኩ በማከናወን ውጤታማ መሆን የሚያስችል በተግባር የተረጋገጠ የጃፓኖች ፍልስፍና ነው፡፡ በ2004 ዓ.ም የተቋቋመው የኢትዮጵያ ካይዘን ኢንስቲትዩት በመንግስታዊ ተቋማት የካይዘንን ፍልስፍና ለማስረጽ ሲሰራ መቆየቱን ዋና ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል፡፡ በ2010 ዓ.ም በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ 240 አምራች እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የመጀመሪያ ደረጃ ካይዘን መተግበር ጀምረዋል፡፡ ካይዘንን በመተግበራቸው ተቋማቱ ምርታማነታቸው እየጨመረ እንደመጣ የገለጹት ዳይሬክተሩ በተለይም ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ወጪ ቆጣቢ አሠራርን በማስፈን ለውጥ ማስመዝገብ ችለዋል ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ካይዘን ኢንስቲትዩት በሰራው ስራ በተቋማቱ 2 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ከብክነት ማዳኑን ዳይሬክተሩ ይናገራሉ፡፡ የተጀመረውን  አገራዊ ለውጥ ለማስቀጠል ኢንስቲትዩቱ በተለይም የማምረቻ ዘርፍን የሚደግፉ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ እንደሆነ ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡ ለችግር ፈቺ የምርምር ስራዎች ትኩረት ሰጥቶ መስራት የኢንስቲትዩቱ ሌላው ትኩረት እንደሆነ የገለጹት አቶ መኮንን ያየ በጃፓን መንግስት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በ730 ሚሊዮን ብር የልህቀት ማዕከል ለማስገንባት ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን አመልክተዋል፡፡ ይህም ኢንስቲትዩቱ ከአገር አልፎ ለምስራቅ አፍሪካ አገሮች አቅም እንዲሆን የተያዘውን አገራዊ ራዕይ ለማሳካት እንደሚያግዝ አስረድተዋል፡፡ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አሸሪፍ ሃጂ አኑር በክልሉ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ በሚነሳባቸው ተቋማት በዚህ ዓመት ካይዘንን ለማስጀመር መታቀዱን ገልጸዋል፡፡ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ከመድረኩ ያገኙትን እውቀት በመጠቀም ሠራተኞቻቸውን በማስተባበር በተቋማቸው ለውጥ ለማምጣት እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡ በአሶሳ ከተማ ትናንት በተካሄደው የልምድ ለውውጥ መድረክ 60 የሚደርሱ  የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና የተቋማት ኃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም