በትግራይ ክልል እድገትን ለማስቀጠል የሚያስችል ፍኖተ ካርታ እንደሚዘጋጅ ተገለጸ

143
መቀሌ ግንቦት 14/2010 በትግራይ ክልል ሁለተናዊ እድገትን ለማስቀጠል የሚያስችል ፍኖተ ካርታ እንደሚዘጋጅ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ገለጹ፡፡ የኢፌዴሪ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል በሀገር አቀፍ ደረጃ ያዘጋጀው ፍኖተ ካርታ ከትግራይ ክልል ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ለማጣጣም የሚያስችል የምክክር መድረክ ትናንት በመቀሌ  ከተማ ተጀምሯል። በምክክር መድረኩ የተገኙት ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል እንዳሉት  በሀገር ደረጃ የተዘጋጀው  ፍኖተ ካርታ ከክልሉ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማዋሃድ እድገትን ለማስቀጠልና ለውጥ ለማምጣት ያስችላል። ፍንተ ካርታው በልማት ሂደት ወቅት የሚያገጥምን ችግር ከምንጩ  ለይቶ  የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ፣ በምርምርና ጥናት የተደገፉ ስራዎችን ለማከናወን እንደሚበጅ ተናግረዋል። እንዲሁም የተለመዱ ስራዎችን በመቀየር አዳዲሶችን ለማስፋት ወሳኝ በመሆኑ ከክልሉ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማያያዝ  ፍኖተ ካርታው እንደሚዘጋጅ ገልጸው ለዚህም የምክክር መድረኩ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተናግረዋል። በመድረኩ የተሳተፉት ዶክተር ካሱ ኢላላ በሰጡት አስተያየት የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል በሀገር ደረጃ ያዘጋጀው ፎኖተ ካርታ  ሁለንተናዊ እድገት ለማስቀጠል እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡ የተዘጋጀውም የበርካታ ሃገራት መልካም ተሞክሮን በመጠቀም እንደሆነ ጠቁመው  ለዚህም  የኢትዮጵያ ምሁራን ፣ ከአሜሪካ፣አውሮፓና ከኢስያ የመጡ ባለሙያዎችም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን አስረድተዋል። ፍኖተ ካርታው ሲዘጋጅ ሀገሪቱ  እያካሄደችው ያለውን የልማት ጉዞ ሊያፋጥን ከሚያስችል መመዘኛ ታይቶ የተወሰደ መሆኑንም ጠቅሰዋል። በመድረኩ በፍኖተ ካርታው ከተመለከቱት ጉዳዮች መካከል በግብርና ባዮቴክኖሎጂ ዘርፍ በዋነኛነት የአትክልትና ፍራፍሬ፣የዝርያ ማሻሻያና ብዜት፣የመስኖ ልማት፣ ስርዓትና ስነ-ምግብ፣የእንስሳት በሽታ ነፃ ቀጠና ምስረታ ላይ ውይይት ይደረጋል፡፡ በኢንዱስትሪ ባዮቴክኖሎጂ ዘርፍ ላይ ደግሞ ከስኳር ፋብሪካዎች የሚገኝ ተረፈ ምርት ወደ ጥቅም የሚቀይር፣በኢንዱስትሪ ዘርፍ የስኳር ኢንዱስትሪያና የስነህይወታዊ ማዳበሪያ ጉዳይ ላይም እንዲሁ፡፡ ለአምስት ቀናት በሚቆየው የምክክር መድረኩ ከፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል፣ከተለያዩ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ፣በክልሉ ከሚገኙ ዩኒቨርስቲዎችና የመንግስት ተቋማት የተውጣጡ ምሁራን እየተሳተፉ ነው። የጤና ባዮቴክኖሎጂ ራሱን ችሎ ፍኖተ ካርታ የተዘጋጀለት ሲሆን፣ በሌሎች  ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ባለሙያዎቹ በመወያየት ተጨማሪ የማዳበሪያ ሃሳቦች ይሰባሰባሉ ተብሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም