ለለውጡ ቀጣይነት በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች በተደራጀ መንገድ ሊንቀሳቀሱ ይገባል - የአዲስ አበባ ኢህአዴግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ

64
አዳማ ጥቅምት 10/2011 በሀገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ በዘላቂነት ለማስቀጠል እንዲቻል በየደረጃው የሚገኘው አመራሮች በተደራጀ መንገድ ሊንቀሳቀስ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ኢህአዴግ ጽህፈት ቤት አሳሰበ። በመዲናዋ ለሚገኙ 2ሺህ የወረዳና ክፍለ ከተማ አመራሮች ለሶስት ቀናት የተዘጋጀ የስልጠና መድረክ ትናንት በአዳማ ገልመ አባገዳ አዳራሽ ተጀምሯል። የአዲስ አበባ ኢህአዴግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ በወቅቱ እንዳሉት በሀገሪቱ የተፈጠረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ለማስቀጠል ኢህአዴግ በልዩ ትኩረት እየሠራ ነው። በተለይ ለውጡን ከዳር ለማድረስ አመራሩ በተናጠል ከመሥራት ይልቅ በተደራጀ አግባብ ሊንቀሳቀስ እንደሚገባ አሳስበዋል። ህብረተሰቡ ከመንግስት አስተዳደር የተሻለ ነገር የማግኘት ፍላጎት እያደገ መጥቷል ያሉት አቶ ተስፋዬ ይህን ፍላጎት ለማሟላት የምንገኝበትን የለውጠ ሂደት አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡ ኢህአዴግ በ11ኛው ጉባኤ ላሳለፋቸው ውሳኔዎች ተፈፃሚነት በግንባር ቀደም ከመንቀሰቀስ ባለፈም ጉባኤው ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት እንዲመሩም አስገንዝበዋል። በዚህ ላይ የጋራ ግንዛቤና ግልፅነት ለመፍጠር ታስቦ መድረኩ መዘጋጀቱን ጠቁመው ለውጡንም በብቃት ለመምራት ተቋማዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ በለውጡ እንቅስቃሴ ውስጥ አመራሩ በጥበብና በዕውቀት እየተመራ የሚፈለገው ውጤት እንዲመጣ ስልጠናው አቅም እንደሚፈጥር አስታውቀዋል፡፡ ''በአዲስ አበባ ብዙ አንገብጋቢ ጥያቄዎች አሉ'' ያሉት ሃላፈው ለጥያቄዎቹ በወቅቱ ምላሽ ለመስጠት የሚችሉ አዳዲስ አመራሮች በብዛት ተመልምለው መመደባቸውንም አስታውቀዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም