በትግራይ ክልል አገር አቀፍና ክልላዊ ፈተናዎችን ኩረጃ ለማስቀረት ዝግጅት ተደርጓል...የክልሉ ትምህርት ቢሮ

38
መቀሌ ግንቦት 14/2010 በትግራይ ክልል በቅርቡ በሚሰጡ አገር አቀፍና ክልል አቀፍ ብሔራዊ ፈተናዎች የፈተና ኩረጃን ለማስቀረት የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ። የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ገብረመስቀል ካህሳይ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ እንዳሉት፣ በክልሉ የሚሰጡትን ክልላዊና ብሔራዊ ፈተናዎች የተሳካ ለማድረግ ዝግጅት ሲደረግ ቆይቷል። በተለይ በአንዳንድ ተማሪዎች ሊፈጸም የሚችለውን የፈተና ኩረጃ ለማስቀረት ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመው፣ የፈተና ሂደቱን ስኬታማ ለማድረግ ከ10 ሺህ በላይ ፈታኞችና ተቆጣጣሪዎች ፣ የፀጥታ አስከባሪዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት መዘጋጀታቸውን አስረድተዋል። " ኩረጃ ሊወገዝ ይገባል፤ ተማሪዎችን ብቻ ሳይሆን ህዝብና አገርንም የሚያጠፋ የሙስና ተግባር ነው" ያሉት  ኃላፊው፣ ኩረጃን ለማስቀረት ከወላጆች ጀምሮ በየደረጃው ያሉ አካላት በቅንጅት እንዲሰሩ ጠይቀዋል። ተማሪዎችም በሚሰጡ ብሔራዊና ክልላዊ ፈተናዎች ተማሪዎች የራሳቸውን በቂ ዝግጅት አድርገው ፈተናውን በጥንቃቄ እንዲሰሩ አሳስበዋል። የ8ኛ፣10ኛ እና 12ኛ ክፍል ፈተናዎች በክልሉ በተዘጋጁ 400 የመፈተኛ ጣቢያዎች እንደሚሰጡና በሦሶስቱም ፈተናዎች በአጠቃላይ 240 ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎች እንደሚፈተኑም ዶክተር ገምረመስቀል አስረድተዋል። እንደእርሳቸው ገለጻ ዘንድሮ ለአገርና ክልል አቀፍ ፈተና የሚቀርቡ ተማሪዎች ቁጥር ካለፈው ዓመት ተፈታኞች ቁጥር ጋር ሲነጻጸር በ22ሺህ ብልጫ አሳይቷል። በክልሉ የትምህርት ቤቶች ቁጥር ዘንድሮ መጨመሩ ለተፈታኝ ተማሪዎች ቁጥር መጨመር ዋነኛ ምክናያት መሆኑንም ገልጸዋል ፡፡ ከአጣላይ ተፈታኞች መካከልም ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ሴት ተማሪዎች መሆናቸው ነው የተናገሩት። በፈተናው ከሚቀመጡ አጠቃላይ ተማሪዎች መካከልም 16ሺህ የሚሆኑት የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ተፈታኞች መሆናቸውንም አመልክተዋል። እንደዶክተር ገብረመስቀለ ገለጻ፣ የሮመዳን ጾምን ምክንያት በማድረግ በተያዘው ግንቦት ወር መጨረሻ በክልል ደረጃ ሊሰጥ የነበረው የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተናን ተራዝሞ ከሰኔ 11 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ለሦስት ቀናት እንዲሰጥ ተወስኗል። በክልሉ ዘንድሮ የትምህርት ተደራሽነትን ለማሳደግ በተደረገው ጥረት የተማሪዎችን ቁጥር ማሳደግ መቻሉን  ከክልሉ  ትምህርት ቢሮ  የተገኘው መረጃ  ያመላክታል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም