በትግራይ ክልል የማእድን ልማትን ለማዘመን የሚያስችል የስልጠና መርሃ ግብር ሊጀመር ነው

70
መቀሌ ጥቅምት 10/2011 በጥቃቅና አነስተኛ ተቋማት በተደራጁ ወጣቶች በባህላዊ መንገድ እየተካሄደ ያለውን የማእድን ልማት ለማዘመን  ከደረጃ አንድ እስከ ደረጃ አምስት የስልጠና መርሀ ግብር ለመጀመር መዘጋጀቱን የትግራይ ክልል ቴክኒክ፣ ሙያና ትምህርት ስልጠና ቢሮ አስታወቀ። የቢሮው  ኃላፊ ዶክተር ሙሉጌታ ሓዱሽ እንደገለፁት በተያዘው በጀት አመት ከክልሉ የተውጣጡ ከ100 በላይ ወጣቶችን በመቀበል ስልጠናውን ለመጀመር  ዝግጅት ተደርጓል ። ስልጠናው በባህላዊ መንገድና በጉልበት ሲካሄድ የነበረውን የወርቅና የሌሎች ማእድናት ፍለጋ ስራ በሰለጠነ የሰው ሃይል እንዲታገዝ  ዓላማ ያደረገ ነው። በማእድን ትምህርት ከተሰማራውና "ስቴም" ከተሰኘ የካናዳ ድርጅት ጋር በመተባበር ስልጠናው እንደሚሰጥ ተናግረዋል ። አስረኛ ክፍል ያጠናቀቁና የኮሌጅ ትምህርታቸውን ያቋረጡ ተማሪዎች ተደራጅተው በስልጠናው ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አመላክተዋል ። "ሀላፊው እንዳሉት ስልጠናውን ለመጀመር የመምህራን ምልመላ፣ የስልጠና ማእከል  ማደራጀትና ተጓዳኝ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ ነው" ብለዋል ። በማእድን ዓይነቶች  መለየት፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በስራ ላይ አደጋ መከላከልና ጥንቃቄ፣ በእቅድ ዝግጅት፣ በስራ ፈጠራና መሰል ዘርፎች በንድፈ ሀሳብና በተግባር የታገዘ  ስልጠና እንደሚሰጥም አብራርተዋል ። "ወጣቶቹ ስልጠናውን ሲያጠናቅቁ የስራና የገበያ ትስስር ይመቻችላቸዋል" ብለዋል ። በሀገሪቱ በሚገኙ የቴክኒክ፣ ሙያና ትምህርት ስልጠና ኮሌጆች በማእድን ዘርፍ ስልጠና አለመሰጠቱ አገሪቱ ከዘርፉ ማግኘ የሚገባትን ጥቅም እንዳታገኝ የራሱን አስተዋፆ ማድረጉን ጠቁመዋል ። የትግራይ ክልል ማእድን ልማት ኤጀንሲ ተጠባባቂ ኃላፊ አቶ መሓሪ ወልደኪሮስ በበኩላቸው ''ስልጠናው ሃገሪቱ በሙያ የተደገፈ የማእድን ልማት በጥራት በማምረት በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ እንድትሆን ያደርጋታል'' ብለዋል። በክልሉ 40 ሺህ ወጣቶች በባህላዊ ዘዴ ወርቅ፣ ሳፋየርና ሌሎች ማእድናት በማምረት ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ በ2010 ዓ.ም ባህላዊ ዘዴን በመጠቀም በተካሄደው የወርቅ ፍለጋ ስራ ከ2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የወርቅ ምርት መገኘቱ ገልጸዋል። በኢትዮጰያ የካናዳ የማእድን ማበልጸጊያና ስልጠና ዳይሬክተር ሚስስ ሬና ጉንድዝ እንዳሉት ''ስልጠናው በዋናነት የክልሉ ሴቶችና ወጣቶችን በማእድን ኢንዱስትሪ ልማት አቅምና ክህሎታቸውን ገንብተው ራሳቸውንና ሃገራቸውን እንዲጠቅሙ ለማስቻል ነው'' ብለዋል። በማእድን ልማት ያለውን የሙያ ክፍተት በዕውቀትና ክህሎት በመደገፍ ወጣቶች በዘርፉ ተሰማርተው ተጠቃሚ ለማድረግ የካናዳ መንግስት በትምህርትና ሙያ ስልጠና ኮሌጆች በሙከራ ደረጃ የአቅም ግንባታ ስልጠናውን እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡ ስልጠናው የማእድን ዘርፍ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በመገንዘብ ከባህላዊ የአመራረት ዘዴ ይልቅ በጥናትና ሙያ፣ በዘመናዊና ቴክኖሎጂ የተደገፈ ፍለጋ ለማካሄድ እንደሚረዳ እምነታቸውን ገልፀዋል፡፡ ለስልጠናው የሚያገለግል ስርዓተ ትምህርት ተቀርጾ ወደ ተግባር መገባቱን የተናገሩት ደግሞ በኢትዮጰያ የካናዳ ፕሮጀክት ቴክኒካል ኤክስፐርት ሚስተር ላስ ኢሪክሰን ናቸው። በትግራይ ክልል ለአምስት ተከታታይ ዓመታት የሚቆየው የሙያ ስልጠና ፕሮጀክቱ በሸሬና አክሱም ቴክኒክ ሙያና ትምህርት ስልጠና ኮሌጆች ውስጥ ይካሄዳል። ውጤቱ እየታየም በመላው የሃገሪቱ ክፍሎች እንዲስፋፋ ይደረጋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም