አዲሱ ካቢኔ በመጪዎቹ 100 ቀናት የህዝቡን ፍላጎት የሚመጥን ለውጥ ለማምጣት እንዲረባረብ ተጠየቀ

110
አዲስ አበባ ጥቅምት 10/2011 የአዲሱ ካቢኔ አባላት በመጪዎቹ 100 ቀናት እቅድ በማዘጋጀት የህዝቡን ፍላጎት የሚመጥን ፈጣን ለውጥ ለማምጣት እንዲረባረቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አሳሰቡ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩትና የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች የተሳተፉበት የሁለት ቀናት ስትራቴጂያዊ አውደ ጥናት ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ተጀምሯል። ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ከፍተኛው የአመራር አካል በአገሪቱ የተጀመረውን የለውጥ  ሂደት ለማስቀጠል በማያቋርጥ የመማርና የመተግባር ሂደት ውስጥ መግባት አለበት። አመራሩ በየፊናው በትጋት በመስራትና ውጤታማነትን በማሳየት ለሚመራው ሰራተኛና መላው ህዝብ ምሳሌ መሆን እንዳለበትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍጹም አረጋ በተገኘው መረጃ መሰረት የአውደ ጥናቱ ዋና ዓላማ አሁን በአገሪቱ የተጀመረውን የለውጥ ጎዳና በዘላቂነት በማስቀጠል ውጤት የሚገኝበትን መንገድ መዘየድ ነው። እስከ ነገ የሚቆየው አውደ ጥናት ቁልፍ በሆኑ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ አትኩሮ የሚነጋገር ሲሆን በተመረጡ የዘርፉ ምሁራንም ትምህርታዊ ገለፃ ይደረጋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም