በ40/60 ቤቶች ልማት ፕሮግራም ከ8ሺህ በላይ ቤቶች ግንባታ ሊጀመር ነው

113
አዲስ አበባ ግንቦት 14/2010 በአዲስ አበባ ከተማ በ40/60 ቤቶች ልማት ፕሮግራም ከ8ሺህ በላይ ቤቶች ግንባታ ሊጀመር እንደሆነ የከተማ አስተዳደሩ የቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ አስታወቀ። ኢንተርፕራይዙ ለግንባታው ማስጀመሪያ በቦሌ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ቦሌ አራብሳ በሚባለው አካባቢ 38 ሄክታር መሬት ከከተማ አስተዳደሩ እንደተረከበም ለኢዜአ በላከው መግለጫ ገልጿል። የተረከበው መሬት በ54 ህንጻዎች 8ሺህ428 ቤቶችን ለመገንባት ያስችላል። በግንባታ ሳይቱ ባለ ሁለት ቤዝመንትና ባለ 15 ወለል የሆኑ 40 ህንጻዎች እንዲሁም በተመሳሳይ ባለሁለት ቤዝምንትና ባለ 13 ወለል የሆኑ 14 ህንጻዎች በድምሩ 54 ህንጻዎችን ለመገንባት የዲዛይን ስራ እየተከናነ ነው። ስራውን ለመጀመርም የአማካሪ ድርጅቶች የጨረታ ሰነድ ተከፍቶ የቴክኒክ ግምገማ እየተከናወነ ሲሆን ስራ ተቋራጮችን ለመምረጥ የሚያስችል ማንዋል መጠናቀቁም ተገልጿል። ያልተጠናቀቁ ቅድመ ሁኔታዎችን በማጠናቀቅ የኢንተርፕራይዙ ማኔጅመንት አጽድቆ ወደ ስራ ይገባል። ኢንተርፕራይዙ የግንባታ ስራውን የሚያስፈጽም ተጨማሪ አምስት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችን የከፈተ በመሆኑ በሰው ኃይልና በግብአት አቅርቦት የማጠናከር ስራዎችን እያከናወነ እንደሆነ ተጠቁሟል። በግንባታ ሳይቱ የግብአት አቅርቦት ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት ከብረትና ከሊፍት በስተቀር ኢንተርፕራይዙ ሙሉ በሙሉ ከግንባታ ግብአት አቅርቦት ስራ የሚወጣበት አዲስ የኮንትራት አስተዳደር ስርዓት ተገባራዊ ይደረጋል። ይህም ደግሞ ቀደም ብሎ በተገነቡት የጋራ መኖሪያ ቤቶች እያጋጠመ የነበረውን የግብአት አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ ያስችላል ሲል መግለጫው ያትታል። ስራው በስራ ተቋራጮች የሚከናወን በመሆኑ ኢንተርፕራይዙ  ፕሮጀክቶቹን መምራትና የጥራት ቁጥጥሩ ላይ በትኩረት ይሰራል ተብሎ ይጠበቃል። ለግንባታው የሚውል የብረት ግብአት ለማሟላትም ከ50ሺህ በላይ የአርማታ ብረት በአይነትና በመጠን ተለይቶ የግዥ ሂደት ላይ እንደሆነ ተጠቁሟል። በአዲስ አበባ በሰንጋ ተራና በክራውን ሳይቶች የተገነቡት 972 ባለ አራት፣ ባለ ሦስትና ባለሁለት መኝታ የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች በዕጣ ሐምሌ 1 ቀን 2009 ዓ ም መተላለፋቸው ይታወሳል። በ40/60 ፕሮግራም ከተመዘገቡ 164 ሺህ ቤት ፈላጊዎች መካከል 140 ሺህ የሚሆኑት ቁጠባቸውን በመክፈል ላይ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም