በዓሉ በደቡብ ህዝቦች ክልል በድምቀት እንደሚከበር ተገለጸ

60
ሀዋሳ ግንቦት14/2010  በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል 27ኛው የግንቦት 20 በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት እንደሚከበር የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ገለጸ፡፡ ቢሮው ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው  ሃገሪቱ በለውጥ ጎዳና ባለችበት ወቅት ላይ የደረሰው የዘንድሮው በዓል  ከግንቦት 15/2010ዓ.ም. ጀምሮ በክልሉ ይከበራል፡፡ የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ከግንቦት20 የድል ቱሩፋቶች ተጠቃሚ መሆናቸውንና ከምንም በላይ ማንነታቸው ተከብሮ ህገ መንግስታዊ ዋስትና ያገኙበት እንደሆነ ተመልክቷል፡፡ በዓሉ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች የሚከበረው ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡትን ለውጦች ለማጎልበትና አብሮነትን ያጠናከረውን የፌደራል ስርዓት የሚፈታተኑ ችግሮችን ለይቶ በጋራ ለመፍታት በሚያነሳሱ ዝግጅቶች መሆኑን ቢሮው አስታውቋል፡፡ መንግስት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ያጋጠመውን ጊዜያዊ ችግር ለመፍታት ፣ ዘላቂ ሰላም፣ልማትና ዴሞክራሲ ለማረጋገጥ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ በመሆኑ ህብረተሰቡ ይህንን ተገንዝቦ ከመንግስት ጋር እንዲረባረብም ጥሪ ቀርቧል፡፡ "የላቀ ብሄራዊ መግባባትና ዴሞክራሲያዊ አንድነት ለላቀ ሃገራዊ ስኬት" የሚል መሪ ሀሳብ በፌደራሊዝም ዙሪያ የበለጠ መረዳትና የተሻለ መግባባት የሚፈጥር የፓናል ውይይት ይካሄዳል ተብሏል፡፡ በኪነ ጥበብና በሌሎችም ዝግጅቶች  በዓሉ በድምቀት እንደሚከበር ታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም