የህግ የበላይነትን ለማስከበር የጸጥታ አካላትና ሚዲያ ዋነኛ ባለድርሻ አካላት ሆነው መስራት አለባቸው

69
አዲስ አበባ ጥቅምት 9/2011 በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች የሚታየውን ችግር ለመፍታትና የህግ የበላይነትን ለማስከበር የጸጥታ አካላትና ሚዲያ ዋነኛ ባለድርሻ አካላት ሆነው መስራት እንዳለባቸው ተነገረ። ኢዜአ ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎች እንደተናገሩት፤ በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታትና መንግስት ለህግ የበላይነት መረጋገጥ ቅድሚያ ትኩረት በመስጠት መስራት ይኖርበታል። መንግስት እስካሁን ያስመዘገባቸው ሁለንተናዊ ለውጦች እንዲቀጥሉ ለማድረግ በአገር ደረጃ እየታዩ ያሉትን የህግ የበላይነት የማስከበር ክፍተቶች ማረም እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። መንግስት ጸጥታ ለማስከበርና ሰላማዊ ሁኔታ ለመፍጠር የሚያደርገውን ጥረት በዋነኛነት የጸጥታ ሃይሉና የሚዲያ ተቋማት በኃላፊነት ስሜት መስራት እንዳለባቸው አመልክተዋል። ዜጎች ተዘዋውረው የመስራት መብታቸውን ተጠቅመው ሃብት እንዲያፈሩ ያለስጋት መንቀሳቀስ የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ መፈጠር እንዳለበትም ጠቁመዋል። ህግ ማስከበር በማንኛውም ወቅት ችላ ሳይባል የህብረተሰቡን የስጋት ምንጮች ማድረቅና ህግ የሚጥሱ አጥፊዎችን በህግ ፊት ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል። አቶ በሪሁ ገብረዮሃንስ እንደገለፁት ተዘዋውሮ የመስራት፣ የመንቀሳቀስ እንዲሁም ሃብት የማፍራት ችግሮችን  ቅድሚያ ሰጥቶ በመፍታት ኃላፊነት ያለበት መንግስት ነው ፡፡ እንዲሁም ፖሊስ ፣ የጸጥታ አካላትና ሚዲያ  በጋራ ቢሰሩ የተሻለ ስራ ይሰራል የሚል እምት እንዳላቸው ገልፀው  “ባለንበት ነባራዊ ሁኔታ ግን የህግ የበላይነትን ከማስጠበቅ አንፃር ክፍተቶች ይታያሉ”ብለዋል፡፡ "ህግ የማስከበር ጉዳይ ላንድ አፍታም ቸል ሊባል አይገባም ህብረተሰቡ በስጋት ውስጥ መኖር የለበትም ምክንያቱም አጥፊዎች ለህግ መቅረብ አለባቸው ፤በዚህ ሁኔታ ላይ ምንም ድርድር መኖር የለበትም ህብረተሰቡ ራሱ ወንጀለኞችን በጉያው ውስጥ ደብቆ ሊሸሽግ አይገባም ሊተባበርም አይገባም በማናቸውም መንገድ ሊታገላቸው ነው የሚገባው “ ያሉት ደግሞ አቶ ዮሴፍ ካሳሁን ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ 'ደመወዝ ይጨመርልን' በሚል ወደ ቤተ-መንግስት ያቀኑ ወታደሮችን ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ በማሳመን በሰላም መመለሳቸውን አስተያየት ሰጪዎቹ አድንቀዋል። በቀጣይም ወታደሩ ብቻ ሳይሆን ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ለመንግስት የሚያቀርበው ጥያቄ ካለው ህጋዊ መንገድን በመከተል መሆን እንዳለበት ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዘመን 4ኛ ዓመት 3ኛ መደበኛ ስብሰባው ላይ በመገኘት ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሳላቸው ጥያቄ ማብራሪያና ምላሽ በሰጡበት ወቅት የግጭት አቅሞችን አስቀድሞ ለማምከንና የህግ የበላይነት ለማስከበር እየተሰራ መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም