የበለጸገች አፍሪካን ለመፍጠር የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ አሁንም ሊጨምር ይገባል-የአፍሪካ ህብረት

93
አዲስ አበባ ጥቅምት 9/2011 ለአፍሪካ ዘላቂ ኢኮኖሚ እድገት አፍሪካውያን ባለሃብቶች የኢንቨስትመን ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ የአፍሪካ ህብረት ጥሪ አቀረበ። ህብረቱ ይህን ያለው ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀራርቦ እየሰራ መሆኑን አስመልክቶ ዛሬ በሰጠው መግለጫ ነው። በአፍሪካ በአጠቃላይ ካለው የግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንት የአፍሪካውያን ተሳትፎ 12 በመቶ ድርሻ እንደሚይዝ መረጃዎች ያሳያሉ። በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የንግድና ኢንዱስትሪ ኮሚሽነር አልበርት ሙቻንጋ እንዳሉት በአፍሪካ ዘላቂ ልማት ለማምጣት የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ አሁንም ሊጠናከር ይገባል። በአህጉሪቷ ኢንቨስትመንትን መጨመር በስፋት የሚስተዋለውን ስራ አጥነት መቀነስ ከማስቻሉ ባለፈ ሰላምና መረጋጋትን ለመፍጠር እንዲሁም ብልጽግናን ለማምጣት እንደሚቻል ተገልጿል። እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ የግል ባለሃብቱ የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ከጨመረ አፍሪካ አሁን እየሄደችበት ካለው የእድገት ደረጃ በፍጥነት ማደግ ትችላለች። በመሆኑም አፍሪካን ወደ መካከለኛ ገቢ ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት የግል ባለሃብቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል። በዚህም ወደ መካከለኛ ገቢ አገሮች ተርታ የምታድግበትን ጊዜ በማፍጠን በዓለም የፖለቲካ ተሰሚነቷ በዚያው ልክ እንደሚጨምር ነው ያብራሩት። ኮሚሽነሩ እንደተናገሩት ኢንቨስትመንት የመልካም አስተዳደርና የአዳዲስ ሃሳቦች መፍለቂያ ጭምር በመሆኑ ከመንግስታት ብቻ አዳዲስ ሃሳቦችን መጠበቅ ተገቢ አይሆንም። "አፍሪካ ልትበለጽግ የምትችለው እኛ አፍሪካውያን ለማደግ ከፈለግን ብቻ ነው" ያሉት ኮሚሽነሩ አፍሪካን ሌላ የውጪ አካል ብቻ እንዲያሳድጋት መጠበቅ የለብንም ሲሉም አጽእኖት ሰጥተዋል። በኢኮኖሚ ያደጉ አገሮች አሁን እያጣጣሙ ያሉት የፖለቲካና የተረጋጋ ህይወት መንግስት ብቻውን ያመጣው ሳይሆን የግሉ ዘርፍ ንቁ ተሳትፎ ጭምር ነው ሲሉም ተናግረዋል። በተለያዩ የዓለም አገራት የሚኖሩ አፍሪካውያን በአህጉራቸው ገንዘባቸውንና ሃሳባቸውን ኢንቨስት እንዲያደርጉ በማበረታታት የኢንቨስትመንት ፍሰቱን ለመጨመር ህብረቱ እየሰራ ነው ብለዋል። የአፍሪካ ወጪና ገቢ (ኤክሲም) ባንክ ፕሬዝዳንት ዶክተር ቤኒዲክት ኦራማህ በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ላይ የተፈረሙ ስምምነቶችን ጨምሮ በሌሎች ጉዳዮች ባንኩ ከህብረቱ ጋር ለመስራት ዝግጁ ነው ብለዋል። በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለሚሰማሩ ባለሃብቶች የብድርና ሌሎች ድጋፎችን ለማድረግ የባንኩ ፍላጎቱ መሆኑንም ገልጸዋል። ነገር ግን የተፈረሙ ስምምነቶችም ሆነ ለግሉ ዘርፍ የሚሰጡ ድጋፎች ለውጥ እንዲያመጡ የግሉ ዘርፍ እድሉን ለመጠቀምና አፍሪካን ለማልማት ቁርጠኛ መሆን እንዳለበት  ገልጸዋል። የአፍሪካ መንግስታት በኢኮኖሚ እድገት የሚያወጧቸውን ፖሊሲዎችም ለግሉ ዘርፍ ተሳትፎ አመቺ እንዲሆኑ አድርገው መቃኘት እንደሚገባቸውም ተገልጿል። ህብረቱ የንግድ አሰራርን ለማዘመን እንዲያስችል የኢንተርኔት ግብይትን ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር እየተፈራረመ መሆኑን ገልጿል። የአፍሪካ ወጪና ገቢ (ኤክሲም) ባንክ ንግድን ለማቀላጠፍ ዲጂታል የክፍያ ስርዓት መዘርጋቱም ተጠቅሷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም