ለቦታ እጥረትና ለገበያ ትስስር ችግሮቻቸውን መፍትሄ እንዲሰጣቸው የሐረር ከተማ ወጣቶች ጠየቁ

71
ሐረር ጥቀምት 9/2011 ''ብድር አግኝተን ወደ ሥራ ብንሰማራም የመሸጫ ቦታ እጥረትና የገበያ ትስስር ማጣት ችግር መፍትሄ ይሰጠን'' ሲሉ በሐረር ከተማ በሥራ ዕድል ፈጠራ የተደራጁ ወጣቶች ገለጹ። ችግሩንም ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ሴቶች፣ህጻናትና ወጣቶች ቢሮ ገልጿል። በክልሉ የታሸጉ ውሃን በማከፋፈል ሥራ ዘርፍ የተደራጀው ወጣት ሰይፈ መኮንን እንደሚናገረው ከአንድ ዓመት በፊት በጀመሩት የታሸገ ውሃ የማከፋፈል ሥራ ግማሽ ሚሊዮን ብር ብድር ወስደው መጀመራቸውን ይገልጻል።በዚህም ካፒታላቸውን ወደ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊየን ብር ማሳደጋቸውንም  ይገልጻል። ሆኖም የመሸጫ ቦታና በተለይ ከመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ጋር የገበያ ትስስር እንዲመቻችላቸው በተደጋጋሚ የሚያቀርቡትን ጥያቄ የሚሰማና በተግባር የሚፈጽም አመራር ባለመኖሩ ካፒታላቸው እየቀነሰና የሥራ ሞራላቸው እየተነካ መምጣቱን ይናገራል። የማህበራቸው ጥያቄያ ምላሽ ቢያገኝ በአጭር ጊዜ ብድራቸውን በመመለስ ለሌሎች አርዓያ ከምንሆንበት ደረጃ እንደርስ ነበር ይላል። ለዶሮ መኖና ለቤት ኪራይ በወር እስከ 42ሺህ ብር እንደሚያወጡ የሚናገረው በዘርፉ  በማህበር  ተደራጅቶ የሚንቀሳቀሰው አስተያየት ሰጪ ወጣት ተሾመ አያሌው፣ ገቢና ወጪያቸው ተመጣጣኝ መሆኑን ይናገራል።ቢያንስ ለቤት ኪራይ የምናወጣውን ገንዘብ ለማዳን የመሥሪያ ቦታ እንዲሰጠን በተደጋጋሚ ብንጠይቅም፤ ምላሽ አጥተናል ብሏል። የሐረሪ ክልል መንግሥት ችግሩን ቢፈታላቸው በከተማ ግብርና በመሰማራት ውጤታማ ለመሆን እንችላለን ሲልም አስተያየቱን ሰጥቷል። በጅምላ ሸቀጥ የተሰማራው ወጣት ሚፍታህ አብራሂም እንደተናገረው ''የገበያ ትስስር ሳይፈጠርልን በጥረታችን በቀን እስከ አምስት ሺህ ብር እንሸጣለን፤ ሆኖም ሰርተን ለቤት ኪራይ ስለምንከፍል ለውጥ ልናመጣ አልቻልንም።'' የክልሉ መንግሥት ችግሩን ለመፍታት በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባ አሳስቧል። የክልሉ ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሐናን ዱሪ  ለቢሮው የተወሰኑ ኢንተርፕራይዞች የገበያ ትስስርና የመሸጫ ቦታ ጥያቄ በተደጋጋሚ እንደሚያቀርቡ ገልጸው፣ ጥያቄዎቹም ምላሽ ያላገኙት የክልሉ ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ተቀናጅተው ባለመሥራታቸው ነው ብለዋል። በዘርፉ የሚታዩትን የአፈጻጸም ጉድለቶች ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል። የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተር የክልሉ ከተማ ልማት ቢሮ  ኃላፊዎች በጉዳዩ ላይ ለማነጋገር የተደረገው ጥረት ምላሽ ሳያገኝ ቀርቷል። የፌዴራልና የሐረሪ ክልል መንግሥታት  ባለፈው በጀት ዓመት ለወጣቶች በመደቡት 40 ሚሊየን ብር ከአንድ ሺህ በላይ ወጣቶች ባገኙት ብድር ሥራ ፈጥረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም