መንግስት የጀመራቸው የልማት ውጥኖች እንዲሳኩ የበኩላችንን እንወጣለን፡- የአዲስ አበባ ነዋሪዎቸ

55
አዲስ አበባ ጥቅምት 9/2011 የኢትዮጵያ መንግስት በተለያዩ ምክንያቶች የገጠመውን የበጀት ጫና በመቋቋም የጀመራቸውን የልማት ውጥኖች ለማሳካት የቀየሰውን አቅጣጫ እንደሚደግፉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ ትናንት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው የመንግስት ተግባራትን የተመለከተ ማበራሪያ በሰጡበት ወቅት "የፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኞች የደሞዝ ጭማሪና የደረጃ ማስተካከያ የት ደረሰ?" የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ምክንያቶች  በመንግስት በጀት ላይ ከፍተኛ ጫና እየተፈጠረ መሆኑን ገልፀዋል። በተለይ ባለፉት ዓመታት በተለያዩ አካባቢዎች የአየር መዛባት ባስከተለው ድርቅ  መንግስት ለበርካታ ዜጎች መሰረታዊ ፍላጎት እያሟላ እንደሚገኝ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል። ከዚህም ሌላ ኢትዮጵያ ለግዙፍ ፕሮጀክቶች እና ሌሎች ታላላቅ አገራዊ ልማቶች ከውጪ አገራት የተበደረችው ገንዘብ የመክፈያ ጊዜ እየተቃረበ መምጣቱንም አክለዋል። እነዚህና ሌሎች አገራዊ ክስተቶች የፈጠሩት የበጀት ጫና ለመንግስት ሰራተኞች የደመወዝ ጭማሪ እና የደረጃ ማስተካከያ  እንዳይደረግ ጫና መፍጠራቸውን ገልጸዋል። በዚህ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ችግሩን መገንዘባቸውን ይገልፃሉ። በመሆኑም አገሪቱ የተጋረጠባትን ከፍተኛ የበጀት ጫና ለመቋቋም በሚደረገው ጥረት ከመንግስት ጎን ቆመው በኃላፊነት እንደሚሰሩ ነው የተናገሩት። አገሪቱ የጀመረችው ለውጥ በስኬት ከቀጠለ ሁሉም ተጠቃሚ እንደሚሆን በመገንዘብ ከመንግስት ጎን በመሆን ሁላችንም ለአገራችን ቅድሚያ ሰጥተን ህዝባችን  ማገልገል አለብን ከዚያ በሚፈጠረው ኢኮኖሚያዊ አቅም ሁላችንም ተጠቃሚ እንሆናለን የሚለው ወጣት አብዱሰላም ሀሰን ነው ፡፡  ለሀገር ልማት አንድ ትውልድ መስዋትነት መክፈል አለበት ያሉት ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ጥላሁን ልንገሬ  በጀትን ለደሞዝ ሳይሆን ለልማት መዋል አለበት ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የተፈጠረው የበጀት ጫና ሲስተካከል በቀጣይ ጥናትን መሰረት ባደረገ መልኩ ለፐብሊክ ስርቪስ ሰራተኛው የደመወዝ ማሻሻያ እንደሚደረግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨምረው መግለጻቸውም ይታወሳል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም