አየር መንገዱ ወደ ኬንያ ተጨማሪ በረራ ሊጀምር ነው

56
አዲስ አበባ ግንቦት 14/2010 የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቀጣዩ ወር ጀምሮ ወደ ኬንያ ተጨማሪ በረራ ሊጀምር ነው። በረራው የሚጀመረው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቅርቡ በኬንያ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ከፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር በደረሱት ስምምነት መሰረት ነው። ሁለቱ መሪዎች የኢትዮጵያ አየር መንገድና የኬንያ አየር መንገድ በትብብር እንዲሰሩ ከመግባባት ላይ ደርሰው ነበር፡፡ በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቱሪዝም መዳረሻ ወደሆነችው ሞምባሳ በሳምንት አንድ ጊዜ የነበረውን በረራ ከሰኔ 17 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በሳምንት ሁለት ጊዜ እንደሚያደርግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ናይሮቢ ሳምንቱን ሙሉ በረራ እንደሚያደርግ ይታወቃል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ላይ ከስምምነት ከተደረሰባቸው ጉዳዮች መካከል ሌላኛው የእስረኞች መፈታት ነው። በእስካሁኑ ሂደት የኬንያ የኢምግሬሽን ባለስልጣንና ናይሮቢ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የዜጎችን ዝርዝር የመለየት እና የጉዞ ሰነድ ዝግጅት እያደረገ ሲሆን እንደተጠናቀቀ ወደ አገር ቤት እንደሚመለሱ ጽህፈት ቤቱ ገልጿል። መንግስት ቀደሞ ሲል 2 ሺህ 500 ዜጎችን ከሱዳን እና ከሳዑዲ አረቢያ ማረሚያ ቤቶች ማስፈታቱ የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም