የመማር ማስተማር ሥራው ሰላማዊ እንዲሆን ኃላፊነታችንን እንወጣለን-በድሬዳዋ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች

56
ድሬዳዋ ጥቅምት 9/2011 በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ሥራው ሰላማዊ እንዲሆን ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ተናገሩ። ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ሂደቱን ሰላማዊና ውጤታማ ለማድረግ በሚያከናውናቸው ተግባራት ላይ ከአስተዳደሩ የሃይማኖት አባቶች ፣ ከአባ ገዳና የዑጋዝ ተቋማት እንዲሁም ከሀገር ሽማግሌዎችና ከፀጥታ አካላት ጋር ተወያይቷል፡፡ በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው በተያዘው ዓመት ሰላማዊና ስኬታማ የመማር ማስተማር ሥራ እንዲያከናውን የበኩላቸውን እገዛ ያደርጋሉ። ከኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ተወክለው የመጡት ሊቀብርሃናት ቀለመወርቅ ቢምረው ወደ ዩኒቨርሲቲው የሚመጡ ተማሪዎች በትምህርታቸው  ውጤታማ እንዲሆኑ ከነሱ ጋር በየጊዜው በመገናኘት ምክር ለመለገስ ተዘጋጅተዋል። " አዳዲስ ተማሪዎችን በፍቅርና በጋራ በመቀበል ጠንክረው እንዲማሩ እንሰራለን፤ በቆይታቸውም የመጡበትን ዋና ዓላማ እንዲያሳኩና ለሰላምና ለሀገራዊ ለውጥ እንዲተጉ እንመክራለን " ብለዋል፡፡ "ሁለት ልጆቼን በጎንደርና በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ልኬ ሳስተምር በዩኒቨርሲቲውና በአካባቢው ማህበረሰብ ላይ ተስፋ ጥዬ ነበር፤ ወደ ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የሚመጡ ተማሪዎችም በኛ ላይ ትልቅ እምነት አላቸው" ያሉት ደግሞ አቶ አሊ ሙሳ ናቸው፡፡ " ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ ያለችግር መጥተው መማር እንዲችሉ የድርሻዬን እወጣለሁ" ብለዋል። አቶ መሐመድ ሀሰን በበኩላቸው አዳዲስ ተማሪዎች በሀገሪቱ እየተኪያሄደ በሚገኘው የለውጥ ሂደት ውስጥ በተስተዋሉ የሰላም ችግሮች ሳይደናገጡ ወደተመደቡበት ተቋም መሄድ እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡ ከእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የመጡት ኡስታዝ ኢዮብ ሐሰን በበኩላቸው ለመማር ማስተማሩ እንቅፋት የሚሆኑና የተማሪዎችን ተልዕኮ የሚያሰናክሉ በዩኒቨርሲቲው ዙሪያ ባሉ የሺሻና ጭፈራ ቤቶች ላይ ተገቢ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ ጠንክረው እንደሚሰሩ ገልጸዋል። " ተማሪዎች ወደአልባሌ ስፍራ እንዳይሄዱና በዩኒቨርሲቲው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራ እንዲከናወን በፍቅርና በመቻቻል ላይ ግንዛቤያቸውን በማሳደግ ኃላፊነቴን እወጣለሁ" ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ለተማሪዎቹ የቅሬታ ምንጭና ለሰላም መደፍረስ ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉትን የሕክምና፣ የመኝታ፣ የምግብና፣ የውሃ አቅርቦት ማስተካከል እንዳለበት የጠቆሙት ደግሞ አቶ አብዶ ኡመር የተባሉ የውይይቱ ተሳታፊ ናቸው። መምህራንም ተማሪዎች ለሚያነሷቸው ቅሬታዎች ፈጣን መፍትሄ በመስጠት ለመማር ማስተማሩ ሰላማዊነት መስራት እንዳለባቸው አመልክተዋል ፡፡ የውይይት መድረኩን የመሩት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ኢብራሂም ኡስማን በበኩላቸው በተቋሙ አስተማማኝ የመማር ማስተማር ስራ እንዲከናወን ማህበረሰቡ፣ የሃይማኖትና የሀገር ሽማግሌዎች፣ የአባ ገዳና ዑጋዝ ተቋማት የማይተካ ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል። "አስተዳደሩም ከዩኒቨርሲቲው ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው ወደ ዩኒቨርሲቲው የሚመጡ ነባርና አዳዲስ ተማሪዎችን በፍቅር ለመቀበልና ለማስተናገድ በየደረጃው ያሉ ነዋሪዎች የሚሳተፉበት ኮሚቴ ተዋቅሮ ይሰራል" ብለዋል፡፡ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ያሬድ ማሞ በበኩላቸው ተቋሙ ከመቼውም ጊዜ ባለይ የመማር ማስተማሩ ሂደት ሰላማዊና የተሳካ እንዲሆን የውስጥ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ተናግረዋል። ተቋሙ ከአስተደዳሩና ከሕብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት የሚፈለገው ውጤት እንዲመጣ በትኩረት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል፡፡ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ከጥቅምት 9 እስከ 11 ቀን 2011 ድረስ 10 ሺህ ነባር ተማሪዎችን አንዲሁም ከጥቅምት 15 ጀምሮ ለተከታታይ አራት ቀናት  4ሺህ 200  አዳዲስ ተማሪዎችን እንደሚቀበል ታውቋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም