ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ሂደቱን በሰላማዊ መንገድ ለማካሄድ መዘጋጀቱን አስታወቀ

39
አክሱም ጥቅምት 9/2011 የዘንድሮውን የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሂደት በሰላማዊ መንገድ ለማካሄድ ዝግጅት ማጠናቀቁን  የአክሱም ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ። በዩኒቨርሲቲው የተመደቡ አዲስ ተማሪዎችን ለመቀበል እየተሰናዳ መሆኑን ገልጿል። የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ኪሮስ ጉዕሽ ለኢዜአ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው የዘመኑን ትምህርት ያለ ምንም ችግር ለማከናወን ከአስተዳደር፣ከኅብረተሰቡ፣ ከተማሪዎች አስተዳደርና ኅብረት ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው። በዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም ለሚነሱ ችግሮች መንስዔ ለሆኑት የመልካም አስተዳደር ችግሮች መፍትሄ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል፤የተማሪዎችን ፍላጎት ባማከለ መልኩ በዘመናዊ አሰራሮች እንደሚሰራ አስረድተዋል። በዚህ ዓመት በዩኒቨርሲቲው የተመደቡ ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጅት መጠናቀቁን ምክትል ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች አቀባበል ኮሚቴ አባል አቶ ኪዳነ ብርሃነ በበኩላቸው ተማሪዎቹ የአካባቢውን ባህል መሠረት ባደረገ መንገድ እንቀበላለን ብለዋል።በተለይም አዲስ ገቢ ተማሪዎችን በብሄሮች፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች አልባሳትና ጭፈራዎች ለመቀበል መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል፡፡ ተማሪዎቹ ከከተማዋ መናኸሪያ ተቀብለው ወደ ዩኒቨርሲተው ግቢ ለማድረስ ተሽከርካሪዎች መመደባቸውን አስታውቀዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ኅብረት ጸሐፊ ተማሪ ገብረሕይወት አባዲ በበኩሉ ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች የሚገለገሉባቸው መኝታ ቤቶች፣ መመገቢያ አዳራሾችና ቤተ መጻህፍት በሚያስፈልጓቸው ግብዓቶች የማሟላትና የማሻሻያ ሥራዎች እንደተከናወኑላቸው ገልጿል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም