ባለስልጣኑ በሩብ ዓመቱ ለመሰብሰብ ካቀደው ግብር 98 በመቶውን ማሳካት ችሏል

60
አዲስ አበባ ጥቅምት 9/2011 የአዲስ አበባ ገቢዎች ባለስልጣን በሩብ ዓመቱ ለመሰብሰብ ካቀደው ግብር 98 በመቶውን ማሳካት መቻሉን አስታወቀ። ባለስልጣኑ የሩብ ዓመቱን የገቢ አፈጻጸም አስመልክቶ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሺሰማ ገብረስላሴ እንደገለጹት ባለስልጣኑ በሩብ ዓመቱ 8 ነጥብ 53 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 8ነጥብ44 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ ችሏል። ይህም የእቅዱ 98 ነጥብ 95 በመቶ ሲሆን ከለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፃር የ21 በመቶ እድገት ያሳየና የተሰበሰበው ግብር ዝቅተኛ ንግድ ላይ ከተሰማሩ የደረጃ "ለ" እና "ሐ" ከፋዮች መሆኑን ገልጸዋል። በግብር አሰባሰብ ወቅት የታክስ መረጃ ጥራት ችግር፣ የታክስ ቴክኖሎጂዎች የታለመላቸውን ዓላማ ለማሳካት ውስንነት መኖራቸው፣ በደረሰኝ ላይ የተመሰረተ ግብይት ማስፈጸም አለመቻልና ከግብር ከፋዩ የሚቀርቡ ቅሬታዎችን ፍጥኖ አለመፍታት ከተስተዋሉ ችግሮች መካከል ናቸው። በተለይ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ ክትትል፣ ቁጥጥር፣ አጠቃቀም፣ ዕድሳትና ምርመራ ውጤታማነት ውስን መሆን ሌላው በግብር አሰባሰቡ ላይ የታየ ችግር ነው። ስለሆነም በቀጣይ ችግሮቹን ለመፍታት ተቋማዊ ገጽታን የመገንባት፣ አሰራሮችን ግልጽ የማድረግ፣ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት የመስጠት እንዲሁም ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር ይበልጥ የመቀራረብና የመመካከር ሥራ በትኩረት ይሰራሉ ሲሉም ተናግረዋል። የጥቅምት ወሩ የደረጃ "ሀ" ግብር ከፋዮች የሚከፍሉበት መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ እነዚህ የንግዱ ህብረሰብ ግብራቸውን በጊዜ እንዲከፍሉም ጠይቀዋል። ባለስልጣኑ በቀን ገቢ ግምት የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታትም የተለያዩ ስራዎች እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቅሰው የንግዱ ማህበረሰብም የሒሳብ መዝገብ በታማኝነት የማቅረብ፣ የሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት የማስወገድና በመጨረሻ ሣምንት ግብር የመክፈል ልማዱን መተው ይገባል ሲሉ አብራርተዋል። የአዲስ አበባ አስተዳደር በ2011 በጀት ዓመት ካቀደው 44 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ውስጥ 34 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ወይም 77 በመቶ ከታክስ የሚሰበሰብ መሆኑ ከባለስልጣኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። በከተማዋ 214 ሺህ ግብር ከፋዮች እንዳሉም መረጃው ገልጿል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም