በደቡብ ክልል ከ52 ሺህ በላይ የሕብረተሰብ ክፍሎች ለሕዳሴው ግድብ በተዘጋጀ የሩጫ ውድድር ላይ ይሳተፋሉ

118
ሀዋሳ 14/2010 በደቡብ ክልል ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ድጋፍ ለማድረግ በተዘጋጀ የሩጫ ውድድር ከ52 ሺህ በላይ የሕብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሳተፉ የክልሉ የሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡ የጽህፈት ቤቱ ዳይሬክተር አቶ ፋሲካ ጌታቸው ትናንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳሉት " ስለ አባይ እሮጣለሁ " በሚል የተዘጋጀው ሩጫ ግንቦት 19 በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በተመሳሳይ ርቀት፣ ቀንና ሰዓት ይካሄዳል፡፡ ለእዚህም በክልሉ በሩጫው ለመሳተፍ የተመዘገቡ 52 ሺህ 568 የሕብረተሰብ ክፍሎች በተለያዩ 63 ማዕከላት ለመሮጥ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡ "የሩጫ ውድድሩ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ 7ኛ ዓመት በዓል አከባበር አካል ነው" ያሉት አቶ ፋሲካ  ሕብረተሰቡ የአጀንዳው ባለቤት በመሆኑ በቀዳሚነት ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን አመልክተዋል። በሩጫው ከ52 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ዳይሬክተሩ ጠቁመው፣ የሩጫ ውድድሩን የተሳካ ለማድረግ ከክልል እስከ ወረዳ የተለያዩ አደረጃጀቶችን በማስተባበር በቂ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡ አቶ ፋሲካ እንዳሉት፣ ቀደምሲል በሩጫው 46 ሺህ የሕብረተሰብ ክፍሎች ይሳተፋሉ ተብሎ በዕቅድ ቢያዝም በአሁኑ ወቅት የተሳታፊዎችን ቁጥር ከ52 ሺህ በላይ በማድረስ አፈጻጸሙን ከመቶ በላይ ለማሳካት ተችሏል፡፡ ሕብረተሰቡ አሁንም በሩጫው የመሳተፍ ፍላጎት ያለው በመሆኑ በየአካባቢው ያሉ የፖስታ አገልግሎት ድርጅቶች እስከመጨረሻው ቀን ድረስ የመሮጫ ከናቲራዎችን ለሽያጭ እንዲያቀርቡ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የሕዳሴው ዋንጫ በክልሉ ሲዘዋወር የነበረውን ከፍተኛ የሕዝብ መነቃቃት በአሁኑ ወቅት አጠናክሮ ለማስቀጠል በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የተለያዩ ሁነቶችን የማዘጋጀት ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ የደቡብ ክልል ርዕሰ መዲና በሆነችው ሃዋሳ በተዘጋጀው የሩጫ ውድድር ላይ ይሳተፋሉ ተብሎ ከሚጠበቁ ከ3 ሺህ በላይ የሕብረተሰብ ክፍሎች መካከል የ5ኛ ክፍል ተማሪዋ መድኃኒት በፍቃዱ አንዷ ናት፡፡ ተማሪዋ ለኢዜአ በሰጠችው አስተያየት ስለ አባይ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የምትሰማው መረጃ ተስፋ እንድትሰንቅ የሚያደርግ በመሆኑ ከጓደኞቿ ጋር ለመሮጥ መዘጋጀቷን ገልጻለች፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በሚዘጋጁ ሩጫዎች የመሳተፍ ልምድ እንዳለው የገለጸው በሃዋሳ ከተማ ፒያሳ አካባቢ በንግድ ሥራ የተሰማራው ወጣት መኮንን በድሉ በበኩሉ ለአባይ የሚሮጠው ጥቅሙ ለጤናም ለአገርም ስለሆነ ሁሉም እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርቧል። " ስለ አባይ መሮጥ በአገር ታሪክ ላይ የራስን ትልቅ አሻራ ማኖር በመሆኑ ከሁለት ልጆቼ ጋር በሩጫው እሳተፋለው " ሲልም የራሱን ተናግሯል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም