በዞኑ ምርታማነትን የማይጨምሩና ጥራት የጎደላቸው የሰብል ዘሮች እንዳይሰራጩ ቁጥጥር እየተደረገ ነው

127
ደብረ ማርቆስ  ጥቅምት 9/2011 በምሥራቅ ጎጃም ዞን ምርታማነትን የማይጨምሩና ጥራት የጎደላቸው የሰብል ዘሮች ተባዝተው እንዳይሰራጩ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ፡፡ የደብረማርቆስ ዕጽዋት ዘርና የግብርና ግብቶች ጥራት ቁጥጥር ኳራንታይን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት እንዳስታወቀው  ምርታማነትን የማይጨምሩና ጥራት የጎደላቸው የሰብል ዘሮች ተባዝተው  ለአርሶ አደሩ እንዳይሰራጩ ትኩረት ተሰጥቶ  እየተሰራ ነው፡፡ የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አለልኝ ነጮ ለኢዜአ እንደገለጹት በሰብል ዘር ጥራት መጓደል ምክንያት የምርታማነትን ችግር እንዳይከሰት ከቡቃያው ጀምሮ ክትትል እየተደረገ ነው። የዘር ጥራቱን ለማስጠበቅ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ችግር ያለባቸውን  ባለሃብቶችም ሆነ አርሶ አደሮች እንዲያስተካክሉ እገዛ ከማድረግ በተጨማሪ ተደጋጋሚ ስህተት እየሰሩ ያሉትን  በዘር ብዜት እንዳይሳተፉ ተደርጓል። ባለፈው ዓመት የበቆሎና የስንዴ ምርጥ ዘርን ከምግብ በቆሎ ጋር የቀላቀሉ እንዲሁም የነቀዘ ዘር ያሰራጩ ሁለት አባዥ ድርጅቶች ከሥራቸው ታግደዋል፡፡ በመስክ የጥራት ፍተሻም ከ87 ሄክታር በላይ የስንዴ እና የበቆሎ ዘር እንዳያልፍ በማድረግ ለ2011 2012 የምርት ዘመን ዘር እንዳይሰራጭ መታገዱን ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡ ጽህፈት ቤቱ በሚያከናውነው የዘር ብዜት ጥራት ቁጥጥር በዞኑ ብቻ ከ3ሺህ 200 ሄክታር በላይ መሬት የለማ  የስንዴ፣የበቆሎ፣የሽንብራ፣የቢራ ገብስና የጤፍ ዘሮችን እየተከታተሉ መሆኑን አስታውቀዋል። የጊወን የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ማህበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ቢያዝን መኮንን እንደገለጹት ዩኒየኑ የአርሶ አደሩን የምርጥ ዝርያዎች እጥረትን ለማቃለልከ120 ሄክታር በላይ በሚሆን ማሳ ላይ  የጤፍ ፥የሽንብራ እና የስንዴ ምርጥ ዘሮችን ጥራታቸውን ጠብቆ እያመረተ መሆኑን ተናግረዋል። የአፍሪ የዘር ብዜት ድርጅት ባለቤት አቶ ሙሉጌታ ስሜነህ በበኩላቸው በ400 ሄክታር ማሳ ላይ የበቆሎና የስንዴ ምርጥ ዝርያዎችን ጥራቱን ጠብቆ በማባዛት በላብራቶሪ ካስተፈሸ  በኋላ  እንደሚያሰራጭ ገልጸዋል፡፡ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ  አበበ መኮንን  መምሪያው ከጽህፈት ቤቱ ጋር ተቀናጅቶ በሚያደርገው የተቀናጀ  ቁጥጥር አርሶ አደሩ ያነሳቸው የነበራቸው የዘር ጥራት ችግሮች እየቀነሱ መምጣታቸውን አስረድተዋል፡፡ ዝርያዎቹ የጥራት ደረጃቸው ጠብቀው የአርሶ አደሩን ጥቅም በሚያረጋግጥ መልኩ ለማቅረብ ጥረቱ እንደሚደረግ ምክትል ኃላፊው አስረድተዋል። ጽህፈት ቤቱ በደብረ ኤልያስ ወረዳ በየጠጋት ቀበሌ የምርጥ ዝርያዎችን የጥራት ደረጃን ለመፈተሽ አባዥ ድርጅቶች፣ የግብርና ባለሙያዎችና አግባብ ያላቸው አካላት በተገኙበት የመስክ የሙከራ ጣቢያዎች ላይ ጉብኝት ተደርጓል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም