በዓለም መድረክ ኢትዮጵያን የሚወክሉ የቦውሊንግ ተወዳዳሪዎች ዝግጅት እያደረጉ ነው

73
አዲስ አበባ ጥቅምት 9/2011 ከሁለት ሳምንት በኋላ በአሜሪካ ላስ ቬጋስ ከተማ በሚካሄደው 54ኛው የዓለም የቦውሊንግ ውድድር ኢትዮጵያ ወክለው የሚሳተፉት ተወዳዳሪዎች አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን የኢትዮጵያ ቦውሊንግ አሶሲየሽን ገለጸ። ውድድሩ ከጥቅምት 23 እስከ ህዳር 3 ቀን 2011 ዓ.ም ይካሄዳል። ኢትዮጵያ በቦውሊንግ ውድድሩ በዘመናይ ነጋና ጌታቸው አለኸኝ ትወከላለች። ቦውሊንግ በእንጨት በተሰራ ወለል ኳስ በመወርወር የተዘጋጁ ኢላማዎችን (ፒኖችን) በመጣል የሚደረግ የስፖርት አይነት ነው። የአሶሲየሽኑ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ይልማ ከፈለኝ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ተወዳዳሪዎቹ ከነሐሴ 15 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በላፍቶ ሞል ሁለገብ የስፖርት ማዕከል ለውድድሩ ዝግጁ የሚያደርጋቸውን ልምምድ እያደረጉ ነው። የቡድኑ አሰልጣኝ ዮሴፍ ሚካኤል ለተወዳዳሪዎቹ በአወራወር፣ ትኩረትን መሰብሰብ፣ የውድድር ዝግጁነትና ሌሎች ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ ድጋፍ እያደረጉላቸው መሆኑን ተናግረዋል። ስፖርተኞቹ  ወደ ደቡብ አፍሪካ ሄደው ስልጠና መውሰዳቸውንና በደቡብ አፍሪካ ያገኙትን ልምድ በሚያድርጉት ልምምድ ላይ ተግባራዊ እያደረጉ እንደሆነም ጠቁመዋል። ተወዳዳሪዎቹ የተመረጡት በሰኔ ወር 2010 ዓ.ም በውድድሩ ላይ የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎችን ለመምረጥ በተካሄደው የግል የበላይነት ውድድር ላይ እንደሆነ ገልጸዋል። የዓለም የቦውሊንግ ውድድር ባለፈው ዓመት በሜክሲኮ ሲካሄድ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገሮች አንደኛ ደረጃ ይዛ እንዳጠናቀቀችና ይህን ተከትሎም ከዓለም አቀፉ የቦውሊንግ ማህበር የስፖርት ቁሳቁስ ሽልማት ማግኘቷን አቶ ይልማ አስታውሰዋል። ኢትዮጵያ ላለፉት አራት አስርት ዓመታት በተለያዩ ዓለም አቀፍ የቦውሊንግ ውድድሮች ላይ በመሳተፍ የተሻለ ተሞክሮና ልምድ እንዳላት ጠቅሳዋል። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ካሉ አገሮች ጋር በቦውሊንግ ጠንካራ ፉክክር እንደምታደርግ ገልጸው በዓለም አቀፍ ደረጃ በስፖርቱ ታዋቂ ከሆኑት አሜሪካና አውሮፓ አገሮች አንጻር ሲታይ ብዙ የቤት ስራ እንደሚቀር ተናግረዋል። ለዚህም በኢትዮጵያ በቂ ለስፖርቱ የሚሆን የማዘውተሪያ ስፍራና ክለቦች መፈጠር ስለሚገባቸው የሚመለከተው አካል አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት አመልክተዋል። የቦውሊንግ ስፖርት በኢትዮጵያ መዘውተር ከጀመረ 50 ዓመታትን እንዳስቆጠረ ይነገራል። በቦውሊንግ ስፖርት ስልጠናዎች በተከታታይ ቢሰጡና የማዘውተሪያ ቦታዎችም በስፋት ቢኖሩ ኢትዮጵያ በዓለም በስፖርቱ ያላትን ደረጃ ማሻሻል እንደምትችል የስፖርቱ አፍቃሪዎች ይገልጻሉ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም