ኢትዮጵያ በሶስተኛው የዓለም የታዳጊዎች ኦሎምፒክ ጨዋታ በስምንት ሜዳሊያዎች 32ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቀቀች

50
አዲስ አበባ ጥቅምት 9/2011 ኢትዮጵያ በሶስተኛው የዓለም የታዳጊዎች ኦሎምፒክ ጨዋታ በስምንት ሜዳሊያዎች 32ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቀቀች። በዚህ ውድድር የተካፈለው የልዑካን ቡድን አባላትም ነገ ወደ ሀገሩ ይገባል ተብሎም ይጠበቃል። ባለፉት 13 ቀናት ከ206 ሀገራት ወደ 4 ሺህ የሚጠጉ ስፖርተኞች  በአርጀቲና ቦነስ አይረስ ከተማ  ሲካሄድ የቆየው  የታዳጊዎች የኦሎምፒከ ጨዋታ ፍጻሜውን አግኝቷል። በዚህ ውድድር በ32 የስፖርት ዓይነቶች  ሲካሄድ የቆየ ሲሆን ኢትዮጵያ 11 አትሌቶችን በአትሌቲክስና በብስክሌት ስፖርት አሳትፋ ስምንት ሜዳሊያዎችን በማግኘት ውድድሯን አጠናቃለች። ኢትዮጵያ ካሳተፈቻቸው 11 አትሌቶች መካከል ዘጠኙ በአትሌቲክስ ስፖርት ተካፍለው ስምንቱን ሜዳሊያ ለሀገራቸው ማምጣት ችለዋል። ከስምንቱ ሜዳሊያዎች መካከል ሁለቱ የወርቅ ሲሆኑ ሁለት የብርና አራት የነሐስ ነው የተገኘው። ለኢትዮጵያ ሁለቱን የወርቅ ሜዳሊያዎች አትሌት አብርሃም ስሜ በ2 ሺህ መሰናክልና አትሌት ጣሰው ያዳ በ800 ሜትር የሩጫ ውድድር ነው ያስገኙት ። የብር ሜዳሊያዎቹን ደግሞ አትሌት በሪሁ አረጋዊ በ3 ሺህ ሜትርና አትሌት መቅደስ አበበ  በ2 ሺህ ሜትር መሰናክል ውድድር ነው ያመጡት። አራቱ የነሐስ ሜዳሊያዎች የተገኙት ደግሞ በ1 ሺህ 500 ሜትር በወንዶች መለሰ ንብረትና በሴቶች ለምለም ኃይሉ፣ እንዲሁም በ3 ሺህ ሜትር አበራሽ ምንሰዎና በ800 ሜትር ሂሩት መሸሻ ናቸው። በዚህ ውድድር የተካፈሉት ቀሪዎቹ ሁለቱ አትሌቶች በብስክሌት ስፖርት የተወዳደሩ ሲሆን ሁለቱም አትሌቶች ድል ሳይቀናቸው ቀርቷል። ኢትዮጵያ ባገኘቻቸው ሁለት የወርቅ ፣ሁለት የብርና አራት የነሐስ ሜዳሊያ ከዓለም 32ኛ ደረጃ ይዛ ነው ያጠናቀቀችው። በሶስተኛው የዓለም የታዳጊዎች ኦሎምፒክ ጨዋታ ከአፍሪካ ግብጽ፣ ደቡብ አፍሪካና ኬኒያ  ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘው ሲያጠናቅቁ ኢትዮጵያ አራተኛ ደረጃን አግኝታለች። በዚህ ውድድር ሩሲያ በ 29 ወርቅ ፣18 የብርና 12 የነሐስ ሜዳሊያ አንደኛ ሆና ስታጠናቅቅ ቻይና 18 የወርቅ፣ ዘጠኝ የብርና ዘጠኝ የነሐስ ሜዳሊያ በመሰብስብ ሁለተኛ ሆና አጠናቃለች። ባለፉት ዓመታት በተደረጉ ሁለት የታዳጊዎች ኦሎምፒክ  ጨዋታ ኢትዮጵያ ተካፍላ የነበረ ሲሆን ከአራት ዓመት በፊት ለሁለተኛ ጊዜ  በቻይና ናንጂንግ በተደረገው ውድድር በ3 ወርቅ፣ በሶስት ብርና በሁለት የነሐስ ሜዳሊያ 16ኛ ደረጃ ይዛ ማጠናቀቋ ይታወሳል። ከስምንት ዓመት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ ሲንጋፖር ባዘጋጀችው ውድድር ደግሞ ሰባት አትሌቶችን በመላክ አምስት ሜዳሊያ በማግኘት 22ኛ ደረጃን ይዛ ነበር ያጠናቀቀችው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም