በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ኢትዮጵያ ቡናና ባህርዳር ከተማ ነገ የፍጻሜ ጨዋታ ያደርጋሉ

120
አዲስ አበባ ጥቅምት 9/2011 በ13ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ነገ ከቀኑ 11 ሰአት ኢትዮጵያ ቡናና ባህርዳር ከተማ  ዋንጫውን ለማንሳት ይጫወታሉ። ከመስከረም 26 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ስታዲየም በስምንት ክለቦች መካከል ሲካሄድ የነበረው ውድድር ነገ ፍጻሜውን ያገኛል። በግማሽ ፍጻሜው ኢትዮጵያ ቡና ጅማ አባጅፋርን ባህርዳር ከተማ መከላከያን በማሸነፍ ነገ ለሚደረገው የፍጻሜ ጨዋታ መድረሳቸው ይታወሳል። በፈረንሳዊው አሰልጣኝ ዲዲየር ጎሜዝ የሚመራው ኢትዮጵያ ቡና በውድድሩ ላይ በአጭር የኳስ ቅብብል ላይ የተመሰረተ ፍሰት ያለው የአጨዋወት ስልት በመከተል ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል። የቡድኑ ተጫዋቾች የክለቡ አሰልጣኝ የሚፈልጉትን የጨዋታ ስልት ለመተግበር የሚያደርጉት ጥረት መልካም ቢሆንም ወጥነት ባለው መልኩ የአጨዋዋት ስልቱን ለመተግበር ጊዜ ሊወስድባቸው እንደሚችል እየተነገረ ነው። በአሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው (ማንጎ) እየተመራ ወደ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ያደገው ባህርዳር ከተማ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ከጨዋታ ጨዋታ ብቃቱን እያሻሻለ የመጣ ቡድን ሆኗል። ቡድኑ በፈጣን መልሶ ማጥቃትና በክንፍ መስመር ላይ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ለተጋጣሚ ቡድኖች ፈታኝ መሆኑን አሳይቷል። የፍጻሜውን ጨዋታ ማሸነፍ ቡድኖቹ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድርን ሲጀምሩ በራስ መተማመንና የአሸናፊነት መንፈስ እንደሚፈጥርላቸው ይገመታል። ከፍጻሜው ጨዋታ በፊት ጅማ አባ ጅፋርና መከላከያ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ላይ የደረጃ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ከጨዋታዎቹ በፊት የአርቲስቶች ቡድንና ሰናይ መስማት የተሳናቸው የእግር ኳስ ክለብ የወዳጅነት ጨዋታ እንደሚያደርጉ የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ያወጣው መርሃ ግብር ያሳያል። ውድድሩ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከመጀመሩ ቀደም ብሎ ክለቦች አቋማቸውን ለመፈተሽና ያለባቸውን ችግር ለመለየት የሚያስችላቸው ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም