ኢትዮጵያ ከጃፓን ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር ትሻለች

138
ጥቅምት 8/2011 ኢትዮጵያና ጃፓን ያላቸውን ረጅም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በማጠናከር በሁለቱ ሀገራት መካከል በሁለትዮሽና በተለያዩ ዘርፎች ያለውን ትብብር ወደ ከፍተኛ ደረጃ ማሸጋገር ይገባል ተባለ፡፡ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ  የጃፓን ፓርላማ ልዑካንን በጽ/ቤታቸው አነጋግረዋል፡፡ ፕሮፌሰር አፈወርቅ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ሁለቱ ሀገራት በንግድና ኢንቨስትመንት መስክ ያላቸውን ግንኙነት ማስፋት እንዳለባቸው ገልጸው፣ ጃፓን ለኢትዮጵያ የምታደርገው የልማት ድጋፍም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል። ጃፓን ለኢትዮጵያ በድርቅ ፣ በሰዎች መፈናቀል፣ መሬት መንሸራተት፣ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች መከላከል፣ ዝግጁነትና ምላሽ ዙሪያ የአቅም ግንባታ ስልጠና የቴክኖሎጂ ድጋፍ እንድታደርግም ሚኒስትር ዴኤታው  ጠይቀዋል፡፡ የጃፓን ፓርላማ ልዑክ መሪ ተሩ ፉኩይ በበኩላቸው ጃፓን ከኢትዮጵያ ጋር በአደጋዎች መከላከልና ዝግጁነት ዙሪያ ትብብር ማድረግ እንደምትፈልግ ገልጸዋል፡፡ ጃፓን በብሄራዊ የመቋቋም ንቅናቄ መርሀ ግብር አማካኝነት  በተደጋጋሚ የተፈጥሮ አደጋዎች የሚከሰቱባት ሀገር ከመሆኗ ጋር ተያይዞ ያካበተችውን ልምድና አቅም ለማጋራት ዝግጁ  መሆኗንም  ተናግረዋል፡፡ መረጃውን  ያደረሰን የውጭ ጉዳይ ቃልአቀባይ ጽ/ቤት ነው።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም