በኢትዮጵያ የተመጣጠነ ምግብ ህክምና በአግባቡ እየተሰጠ አይደለም ተባለ

70
አዲስ አበባ ጥቅምት 8/2011 ኢትዮጵያ ውስጥ በተመጣጠነ ምግብ ህክምና አሰጣጥ ሙያ ዘርፍ የሰለጠነ ባለሙያ እጥረት በመኖሩ ህክምናው በአግባቡ እየተሰጠ አይደለም ተባለ። የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በበኩሉ የባለሙያው መደብ በሆስፒታሎች እንዲኖርና በዘርፉ ያሉ የሚታዩትን ሌሎች ችግሮችን ለመለየት ጥናት እያከናወንኩ ነው ብሏል። ካንሰርን፣ ቲቢንና ስኳርን ለመሳሰሉ ህመሞች ህክምና የሚከታተሉትን ጨምሮ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሳቢያ የጤና እክል ለሚገጥማቸው በተለይም ህፃናት "የተመጣጠነ ምግብ ህክምና" (nutrition therapy) መስጠት የተለመደ የህክምና ተግባር ነው። የተመጣጠነ ምግብ ህክምና ታማሚው በሰውነቱ ውስጥ ያለው የንጥረ ምግብ መጠን፣ ዓይነትና አካላዊ ጉዳት ከተለየ በኋላ በህክምና ባለሙያዎች መመሪያ መሰረት የሚሰጥ የጤና ድጋፍ ነው። በሌሎች ህመሞች ህክምና የሚከታተሉ  የሚሰጣቸውን መደበኛ መድሀኒት ከመውሰድ በተጨማሪ፤ በሽታን የመከላከል አቅማቸውን በተቻለ ፍጥነት በማጎልበት ከህመማቸው በፍጥነት መፈወስ ይችሉ ዘንድ ህክምናው በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑን የመስኩ ሙያተኞች ይገልፃሉ። በተመጣጠነ ምግብ እጥረት በሽታ የሚጠቁ ሰዎች በዋነኝነትም ህጻናት አስቸኳይ የሆነ የተመጣጠነ ምግብ ህክምና ካላገኙ ለሞት ሊዳረጉ ይችላሉ። ለሌሎች በሽታዎች ተብሎ የሚደረግ የህክምና ክትትልም በተመጣጠነ ምግብ ህክምና ካልተደገፈ ውጤታማነቱ አመርቂ አለመሆኑም ይገልፃሉ። በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በስፋት የሚተገበረው የዚህ ዓይነቱ ህክምና በኢትዮጵያ ከጥቂት ሆስፒታሎች በስተቀር ብዙም የተለመደ አይደለም። በአዲስ አበባ የሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ ቲቢ ስፔሻላይዝ ሆስፒታል በአሁኑ ወቅት ህክምናው ከሚሰጥባቸው ጥቂት ሆስፒታሎች መካከል አንዱ ነው። የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ደመቀ መኮንን ለኢዜአ እንደተናገሩት በሆስፒታሉ ተኝተው የሚታከሙ ሰዎች በሰውነታቸው ውስጥ ያለው የንጥረ ምግብ መጠን ተለክቶ የሚሰጣቸው የምግብ ይዘትም እንዲስተካከል ይደረጋል። ለተለያየ የህመም ዓይነት የሚሰጠው የምግብ ህክምናም እንደዛው የተለያየ ነው ብለዋል። ሀኪሞቹ ስራቸውን የሚያከናውኑት ራሱን ችሎ በተዘጋጀ መመሪያ መሰረት በመሆኑ በተመላላሽ የሚታከሙ ህሙማንም ከመድሀኒትና ማድረግ ካለባቸው ጥንቃቄ በተጨማሪ የተመጣጠነ ምግብ ህክምናም ይሰጣቸዋል ብለዋል። ለተለያየ አይነት ህመም የተለያየ አይነት የአመጋገብ ስርዓት አለ መኖሩን የሚናገሩት ዶክተር ደመቀ ይህን  መሰረት የህክምና አገልግሎት ይሰጣል ብለዋል፡፡ በተመሳሳይ አዲስ አበባ ውስጥ ያለው አለርት ሆስፒታልም ይህንን ህክምና ከሚሰጡት መካከል ይጠቀሳል። ለተመላላሽና ተኝተው ለሚታከሙ ህፃናት የተመጣጠነ ምግብ ህክምና እየተሰጠ መሆኑን በሆስፒታሉ የህፃናት ክፍል አስተባባሪ ሲስተር ቅድስት ጌታቸው ይናገራሉ። ከህክምናው በተጨማሪ "ህፃናቱ ምን አይነት አመጋገብን ቢከተሉ በቶሎ ያገግማሉ" በሚል ርእስ ዙሪያ ለወላጆች ትምህርት እንደሚሰጥም አስረድተዋል። ሆስፒታሎቹ ስራቸውን አጠናክረው ለማስቀጠል በተመጣጠነ ምግብ ህክምና የሰለጠነ ባለሙያና የበጀት እጥረት ችግሮች እንዳለባቸው ነው የገለፁት። ሌሎች ሆስፒታሎችም ይህንን ህክምና በመስጠት ታካሚዎች በፍጥነት እንዲያገግሙ ማድረግ አለባቸውም  ነው የጠቆሙት። የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በበኩሉ በጤና ተቋማት ደረጃውን የጠበቀና ከሕክምናው ጋር ተያያዥነት ያለው ምግብ ለማቅረብ እንዲቻል በበጀት አመቱ የዳሰሳ ጥናት ተሰርቶ እንደሚጠናቀቅ ገልጿል። የሚኒስቴሩ የስነ-ምግብ አስተባባሪ አቶ ቢራራ በለጠ እንዳሉት ጥናቱ የተመጣጠነ ምግብ ህክምና እንዳይሰጥ ምክንያት የሆኑ ነገሮችን በመለየት መፍትሄ የሚጠቁም ጭምር ነው። የጥናቱ ምክረ ሀሳብ ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን የተዘጋጀ ሲሆን በተያዘው በጀት ዓመት ተሰርቶ እንደሚጠናቀቅም ገልፀዋል። በሆስፒታሎች በተመጣጠነ ምግብ ህክምና ለተመረቁ ባለሙያዎች የስራ መደብ ባለመኖሩ የሰው ሀይል ፍላጎት ዳሰሳ ጥናት መሰራቱንና በቀጣይ ዘርፉ እንዲስፋፋ አስፈላጊው ይደረጋልም ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም