አዲስ ተሿሚዎች በሀገሪቱ መልካም አስተዳደር፣ ፍትህና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲረጋገጥ ሊሰሩ ይገባል - የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጅ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን

62
አዳማ  ጥቅምት 8/2011 በአዲሱ የሥራ አስፈፃሚ ሹመት ወደ ኃላፊነት የመጡ አመራሮች በሀገሪቱ መልካም አስተዳደር፣ ፍትህና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲረጋገጥ የሚጠበቅባቸው ሚና መወጣት እንዳለባቸው አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጅ ዩኒቨርሲቲ ሴት ምሁራን ገለጹ። በዩኒቨርሲቲው የሥርዓተ ፆታ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና መምህር ዶክተር የሽመቤት ማጆር እንደገለጹት አዲስ ተሿሚዎች ህዝቡን ያማረሩ የመልካም አስተዳደርና የፍትህ እጦት፣ ሌብነትና የተደራጀ ዝርፊያን በማስወገድ ረገድ በቁርጠኝነትና በትጋት መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ አሁን በሀገሪቱ የተጀመረውን ሁሉን አቀፍ ለውጥ ለማስቀጠልና በፅኑ መሰረት ላይ ለማኖር ብሎም ለውጤት እንዲበቃ ለሰለም፣ ልማትና እኩልነት ቅድሚያ በመስጠት መረባረብ እንደሚገባቸውም ተናግረዋል። በጠቅላይ ሚኒስትሩ የካብኔ ሹመት ሴት አመራሮች በመንግስት ስልጣን 50 በመቶ ድርሻ እንዲይዙ መደረጉ ከሀገሪቱ ጠቅላላ ህዝብ ግማሽ ያህሉ የህብረተሰብ ክፍል የሚያነቃቃና ለለውጥ እንዲነሳሳ የሚያደርግ መሆኑንም ዶክተር የሽመቤት አመልክተዋል። ''የተሾሙት ሴት አመራሮች ከዚህ በፊት በየደረጃው ሲመሯቸው በነበረው የክልልና የፌዴራል መንግስት ተቋማት ውስጥ የሚታይ ተጨባጭ ውጤት ያመጡ በመሆኑ ለውጡን ከግብ እንደሚያደርሱ ጥርጥር የለኝም'' ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የኤሌክትሪካል ኢንጅነሪንግ መምህርት መስከረም ታደሰ ናቸው። ''ለውጡ በውጤት የታጀበ ለማድረግና ሀገራዊ ዴሞክራሲያዊ ሽግግሩን ለማፋጠን መንግስት የወሰደው እርምጃ ወቅቱ የሚጠይቀውና ተገቢ  ነው'' ብለዋል። ሹመቱ ሴት አመራሮች ዋና ዋና የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን ጭምር እንዲመሩ ኃላፊነት የተረከቡበትና ወሳኝ የለውጥ ሃይል መሆናቸውን በመንግስት የታመነበት ወቅት መሆኑን ገልጠዋል። አስተማማኝ ሰላም ማስፈን፣ የህብረተሰቡን የፍትህ ጥማት ማርካት፣ ነፃነትና መልካም አስተዳደርን ማረጋገጥ፣ ዋስትና ያለውን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ማድረግ ከአዲሱ አመራሮች የሚጠበቅ ቀዳሚ አጀንዳ ሊሆን እንደሚገባም አስገዝበዋል። በመንግስት የልማት ድርጅቶችና ተቋማት ላይ የሚታየውን የተደራጀ ሌብነትና ዝሪፍያ በማስቆም፣ በማስውገድና መሰረታዊ ለውጥ እንዲመጣ ከማድረግ አኳያ የአዲስ ተሿሚ አመራሮች ቁርጠኝነት የላቀ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው የሪጄስተራር ባለሙያና አካዳሚክ እስታፍ አባል መምህርት ፍፁም ዘሪሁን ናቸው። ''ሴቶች ባላቸው የፖለቲካ ቁርጠኝነትና የሥራ ታታሪነት ያገኙትን የአመራር ዕድል ወደ ተግባር በመቀየር ፍትህ፣ እኩልነትና ዴሞክራሲያዊ አንድነት እንዲመጣ በመስራት ውጤት እንደሚያመጡ እንጠብቃለን'' ብለዋል። ወደ አመራር የመጡ ሴቶች አቅም ያላቸውና ተፅእኖ ፈጣሪ በመሆናቸው በተመደቡበት ተቋማትና የሥራ ዘርፎች ውጤታማ ይሆናሉ የሚል እምነት እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡ እንዲሁም ሀገሪቱን በሁሉም መስኮች ወደ ቀጣይ ምዕራፍ በማሸጋገር ረገድ ለተተኪ ወጣት ሴቶች ምሳሌ ሊሆኑ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም