በድሬዳዋ ጊዜያዊ መጠለያ የነበሩ ተፈናቃዮች ወደተዘጋጀላቸው መኖሪያ መንደር ተጓዙ

76
ድሬደዋ  14/2010 ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው ላለፉት ዘጠኝ ወራት በድሬዳዋ ጊዜያዊ መጠለያ የነበሩ 5ሺ 600 የኦሮሚያ ክልል ተወላጆች በተለያዩ ከተሞች ወደ ተዘጋጀላቸው መኖሪያ መንደር ተጓዙ፡፡ መንግስትና ህብረተሰቡ ላደረጉላቸው ድጋፍና እንክብካቤ ተፈናቃዮች አመስግነው ሁሉም ለሀገር ሰላም መረጋገጥ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አብደላ አህመድ በሺኝት ስነስርዓቱ ላይ እንዳሉት ከመስከረም ሁለት ጀምሮ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው በድሬዳዋ ለተጠለሉት ወገኖች አስተዳደሩ፣ ነዋሪውና ባለሃብቱ ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ በማዋጣት አስፈላጊው  ድጋፍ አድርገውላቸዋል፡፡ ከፊሎቹ ተፈናቃዮች አስቀድሞ በኦሮሚያ ክልል 11 ከተሞች ወደ ተሰሩላቸው መኖሪያ መንደር መጓዛቸውን ገልፀው የቀሩት ደግሞ በተለያዩ ከተሞች ወደተሰራላቸው መንደር በ39 አውቶቢሶች  እንዲጓዙ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ ከተፈናቃዮች መካከል 193 ወጣቶች የተለያዩ የሙያ ሥልጠና ተሰቷቸው  በተለያዩ ፋብሪካዎችና ድርጅቶች ውስጥ እንዲሰሩ  መደረጉን  አቶ አብደላ ጠቅሰዋል፡፡ ቤተሰብና ልጆች ያሏቸው በዕጣ  ከሚያገኙት ቤት በተጨማሪ በቀጣይ ለዘላቂ ሕይወታቸው ማቋቋሚያና  አምራች ዜጋ የሚሆኑበት ድጋፍ መንግስት እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡ እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ 20 ወጣቶችና ጥቂት አዛውንቶች ላቀረቡት ቅሬታ እንደአማራጭ የማቋቋሚያ መንገዶች ተቀይሰው መፍትሄ እንደሚሰጣቸው ነው የገለፁት ፡፡ ''ከዛሬ ጀምሮ ተፈናቃዩች ተጠልለውበት የነበረው የቄራ መጠለያ የተዘጋ ሲሆን በቀጣይ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ይደረጋል''  ብለዋል፡፡ ወደ ተዘጋጀላቸው መኖሪያ መንደር የተጓዙት አቶ ጃይላን ቃሲም በሰጡት አስተያየት የድሬዳዋ ነዋሪና መንግስት ላለፉት ዘጠኝ ወራት ያለመሰልቸት በፍቅርና በርህራሄ ከጎናቸውን በመሆን ላደረጉላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ''ከአሁን በኋላ የማንንም እጅ ሳንጠብቅ እንደቀድሞ ሰርተን መለወጥ ነው የምንፈልገው፤ መንግስት ዘላቂ ኑሯችንን እንድንቀጥል አስፈላጊውን ድጋፍ ሊያደርግልን ይገባል፤ ወደ አዲስ ህይወት የምንጓዝ በመሆኑም የሥነልቦና ምክር ሊሰጠን ይገባል'' ብለዋል፡፡ ወደ አዳማ የተጓዙት ወይዘሮ በድሪያ ያሲን በበኩላቸው ህዝቡ ያለመሰልቸት ለሰጣቸው ድጋፍና ፍቅር አመስግነው መሰል  ጥፋትና ችግር እንዳይፈጠር ህብረተሰቡ ለሰላም መረጋገጥ ተግተው ሊሰሩ  እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ''የሰላምን ዋጋ በሰላም ዕጦት የተሰቃየ ሰው ይበልጥ ይገነዘበዋል፣ ዜጎች ሰላምን ለማረጋገጥ ሁሌም ዝግጁ መሆን አለባቸው'' ብለዋል፡፡ ትናንት ወደ ሻሸመኔ፣ ገላን፣ አዳማ፣ ዱከም፣ ሰበታና ሞጆ የተጓዙት ዜጎች በሶማሌና በኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረ ግጭት ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም