በትግራይ ክልል የሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆኑ ተገለጸ

59
መቀሌ ጥቅምት 8/2011 በትግራይ ክልል የሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን የሦስት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆኑን የክልሉ ዕቅድና ፋይናንስ ቢሮ አስታወቀ። የክልሉ ምክር ቤት አባላት ዕቅዱ በቀሪዎቹ ሁለት ዓመታት የተሻለ አፈጻጸም እንዲኖረው ጊዜያቸውን ሳይሰስቱ መስራት እንዳለባቸው የክልሉ ምክር ቤት አፈጉባኤ ወይዘሮ ቅዱሳን ነጋ አሳስበዋል። የክልሉ የእቅድና ፋይናንስ ቢሮ በዕቅዱ ያለፉት ሦስት ዓመታት አፈጻጸምና የቀሪዎቹ ሁለት ዓመታት ትኩረት አቅጣጫዎችን አስመልክቶ ትናንት የውይይት መድረክ አዘጋጅቷል። በውይይት መድረኩ ላይ የእቅዱን የአፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት በትግራይ ክልል እቅድና ፋይናስ  ቢሮ የእቅድ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ግርማይ ኃይለ እንዳሉት በዕቅዱ ለማከናወን የተያዙ ሥራዎች አፈጻጸማቸው ዝቅተኛ ነው። "በሃገሪቱ ተከስቶ የነበረው አለመረጋጋትን ጨምሮ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት በክልሉ በሁለተኛው የዕቅዱ ዘመን ለማከናወን የተያዙ ሥራዎች አፈጻጸም ዝቅተኛ ሆኗል" ብለዋል። በክልሉ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን በእርሻ፣ በኢንዱስትሪ፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በአገልግሎትና መሰል ዘርፎች ተይዘው የነበሩ እቅዶች አፈጻጸማቸው ከዕቅድ በታች መሆኑንም አቶ ግርማይ ገልፀዋል፡፡ በዕቅዱ አፈጻጸም ላይ በተካሄዱ ጥናቶች የክልሉ የምርታማነት እድገት 9 ነጥብ 36 በመቶ፣ እርሻ 4 በመቶ፣ ኢንዱስትሪ 14 ነጥብ 8 በመቶና ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ደግሞ 17 ነጥብ 7 በመቶ እድገት አስመዝግቧል። ሆኖም "የተመዘገቡ እድገቶች በእቅድ ከተያዘው ጋር ሲነጻጸር አፈጻጸማቸው ዝቅተኛ ነው" ብለዋል ከፍተኛ ባለሙያው። በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረው አለመረጋገትን ጨምሮ የቢሮክራሲ አሰራር፣ የአፈጻጸም ቅልጥፍና እጦት፣ የብድር አቅርቦት ችግር እንዲሁም የመሰረተ ልማት እጦት ለዝቅተኛ አፈጻጸሙ በምክንያትነት ተጠቅሰዋል። "በችግሮቹ ምክንያት በክልሉ ሥራ አጥነትን ወደ 20 በመቶ ከፍ ብሏል" ያሉት ባለሙያው፣ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት አፈጻጸም ድርሻ 3 በመቶ ብቻ መሆኑን ገልጸዋል። የክልሉ የነፍስ ወከፍ ገቢ 796 የአሜሪካን ዶላር ቢደርስም ከድህነት ወለል በታች የሚገኘው የክልሉ ህዝብ ቁጥር ወደ 29 በመቶ ከፍ ማለቱንም ተናግረዋል። በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ በክልሉ የህብረተሰቡ የቁጠባ ልምድ እድገት ማሳየቱን ያስታወሱት አቶ ግርማይ በ2008 ዓ.ም 29 ቢሊዮን ብር፣ በ2009 ዓ.ም ደግሞ ከ40 ቢሊዮን ብር በላይ በቁጠባ ተቀማጭ መደረጉን በማሳያነት ጠቅሰዋል። የባለሃብቶች የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴም የተሻለ አፈጻጸም እንዳለው የተናገሩት አቶ ግርማይ 115 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ የግል ባለሃብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች መሰማራታቸውን ገልጸዋል። ከሦስት ዓመታት ዝቅተኛ አፈጻጸም ትምህርት በመውሰድ በቀሪዎቹ ሁለት ዓመታት የተሻለ ሥራ ለመስራት በተለይ ከምክር ቤቱ አባላት ብዙ እንደሚጠበቅ አስገንዝበዋል። የክልሉ ምክር ቤት አፈጉባኤ ወይዘሮ ቅዱሳን ነጋ በበኩላቸው "የሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የተሻለ አፈጻጸም እንዲኖረው በየደረጃው የሚገኙ የምክር ቤት አባላት ጊዜያቸውን ሳይቆጥቡ መስራት አለባቸው" ብለዋል። "የዕቅዱ ቀሪ ሁለት ዓመታትን የተሳካ ለማድረግ በሁሉም ዘርፎች በተለይ በዴሞክራሲ አቅም ግንባታ ላይ የላቀ ሥራ መስራት አለብን" ብለዋል አፈ ጉባኤዋ። ከክልሉ ምክር ቤት አባላት መካከል አንዳንዶቹ እንዳሉት በቀሪ ጊዜያት የመርሃ ግብሩን አፈጻጸም የተሻለ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። በተለይ የክትትልና ቁጥጥር አሰራርን በማጠናከር ለዕቅዱ መሳካት የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል። ቢሮው ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ በየደረጃው የሚገኙ የክልሉ ምክር ቤት አባላት ተሳታፊ ሆነዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም