በኦሮሚያ ክልል የሰብዓዊ መብት ፎረም ለመመስረት ውይይት እየተካሄደ ነው

64
ቢሾፍቱ ጥቅምት 8/2011 በኦሮሚያ ክልል የሰብዓዊ መብት ፎረም ለመመስረት በፎረሙ አደረጃጀት፣ የአሰራር መመሪያ እንዲሁም ማስፈጸሚያ ስልቶች ላይ የክልሉና የፌዴራል ባለድርሻ አካላት ዛሬ በቢሾፍቱ ከተማ እየመከሩ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በህገ-መንግስቱ የሰፈሩና የአለም አቀፍ ስምምነቶች ተግባራዊ መሆናቸውን ለማረጋገጥ እየሰራ ይገኛል። የስራውን ተፈጻሚነት ለማረጋገጥ በተለያዩ ክልሎች የሰብዓዊ መብት ፎረሞች እያቋቋመ ነው፡፡ ፎረሞቹ ህዝባዊ ንቅናቄን እውን በማድረግ መብቱን የማክበርና የማስከበር ግንዛቤ ያለው ማህበረሰብ መፍጠር፣ በህገ-መንግስቱ መብቶችና ግዴታዎች ላይ ግንዛቤ መፍጠር ለመፍጠር የተለያዩ ስራዎችን ኮሚሽኑ ይሰራል። የግልና የቡድን መብት የሚጠበቅበት ስርዓት እንዲዘረጋም ከባለድርሻ አካላት ጋር ኮሚሽኑ ተቀናጅቶ እንደሚሰራ ተጠቁሟል። የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች የተቋማትን የህዝቡ አጀንዳ በማድረግ መብቶች እንዲከበሩ በማድረግ ተጽእኖ ፈጣሪ እንዲሆኑ ማስቻል የኮሚሽኑ ዓላማ እንደሆነ ኮሚሽነር ዶክተር አዲሱ ገብረእግዚአብሔር ገልጸዋል። በሰብዓዊ መብት ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብሮችን ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን፤ በማረሚያ ቤቶች እና ፖሊስ ጣቢያዎች የተቀናጀ ስራ በማካሄድ ሪፖርቶችን ማውጣቱን ተናግረዋል። ከዚህ ባለፈም በመንደር ምስረታ ፣ መገለልና አድሎ በተመለከተ ግጭት በሚያስከትለው የሰብዓዊ መብት አያያዝ ችግሮች ዙሪያ ጥናቶችን በማካሄድ ሪፖርቱን ይፋ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል። እንደ ዶክተር አዲሱ ገለጻ ፤ የፌዴራልና የክልል መንግስታት ተግባራዊ እያደረጉት የሚገኘው የብሔራዊ ሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሃ ግብር በህገ መንግስቱ የሰፈሩት የህዝቡን መብት በሚያስከብር መልኩ እየሄደ ነው፡፡ በኦሮሚያ ክልል የሚመሰረተው 'የሰብዓዊ መብት ሰራዊት ግንባታ ንቅናቄ ፎረም' አስፈጻሚ አካል ሰብዓዊ መብቶችን በማክበርና በማስከበር እንቅስቃሴ ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲሰራ ከፍተኛ እገዛ እንደሚያበረክት አስረድተዋል። ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የተቋቋመበት አላማ እንዲሳካ ለማድረግ የተደራጀ የህዝብ እንቅስቃሴ እንደሚያስፈልግ አስምረውበታል፡፡ ፎረሙ ተቋቁሞ የሚጠበቀውን ውጤት እንዲያስገኝ ኮሚሽኑ ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ መህቡባ አደም እንዳሉት፤ ፎረሙ መቋቋሙ አሁን የተጀመረውን  አገራዊ የለውጥ ጉዞ የበለጠ እንዲሳካ ከፍተኛ አስተዋጾ ያደርጋል፡፡ በተለይም የህግ የበላይነት እንዲከበር በማድረግ በኩል የላቀ ሚና ያለው በመሆኑ የክልሉ መንግስት የፎረሙ ስራዎች እንዲሳለጡ የበኩሉን ሚና እንደሚጫወት አረጋግጠዋል፡፡ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሃ ግብር ከ2008ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ መደረግ የጀመረ ሲሆን፤ 2012ዓ.ም ድረስ የሚቆይ ይሆናል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም