የሴቶች ወደ ከፍተኛ አመራርነት መምጣት የሀገሪቱን የሰላምና የልማት ውጥኖች ለማሳካት ያግዛል...የድሬዳዋ ነዋሪዎች

82
ድሬዳዋ ጥቅምት 8/2011 አዲሱ የካቢኔ ሹመት ለሴቶች ልዩ ትኩረት መሰጠቱ የተጀመሩ ሀገራዊ የሰላምና የልማት ውጥኖችን በተሻለ ለማሳካት የሚያግዝ መሆኑን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የድሬዳዋ ነዋሪዎች ገለጹ። በአዲሱ የካቢኔ ሹመት የሰላምና የመከላከያ ሚኒስትር መስሪያ ቤቶች በሴቶች መመራታቸው በሀገሪቱ የጠፋውን የሞራልና የሥነ-ምግባር ክፍተቶች ለመድፈን እንደሚያግዝ ተመልክቷል፡፡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከ20 አዳዲስ የካቢኔ ሹመቶች ውስጥ 50 በመቶው በሴቶች እንዲያዝ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ዶክተር አብይ አህመድ የቀረበውን ሹመት ባለፈው ማክሰኞ ተቀብሎ ማጽደቁ ይተዋሳል። በካቢኔ ሹመት አሰጣጥ ላይ ኢዜአ ካነጋገራቸው የድሬዳዋ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ህይወት ልሳነወርቅ እንደገለጹት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከከፍተኛ የስልጣን ቦታዎች ግማሹን ለሴቶች መስጠታቸው የዘመናት የሴቶችን እኩል ተሳትፎና ተጠቃሚነት ጥያቄ በአግባቡ ያረጋገጠ ነው። በአዲስ የተሾሙት ሴት ሚኒስትሮች የወጣቱንና የሴቶችን የሥራ አጥነት ችግር ለመፍታትና ለሰላም እሴት መጎልነት ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩም ጠይቀዋል። ሴቶችን በብዛት ወደአመራርነት በማምጣት በሀገሪቱም ሆነ በአፍሪካ ደረጃ ፈር ቀዳጅ የሆነ የስልጣን ክፍፍል በመደረጉ ደስተኛ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ አቶ አብዱልጀባር ሁሴን የተባሉ የድሬዳዋ ነዋሪ ናቸው፡፡ የሰላም እጦት ሲከሰት ሴቶችና ህጻናት ከማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል በላይ የሚጎዱ እንደመሆናቸው በተለይ ሴት ተሿሚዎች ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥና ለልማት መስራት እንደሚችሉ በተግባር ማሳየት እንዳለባቸው ነው አቶ አብዱልጀባር የተናገሩት፡፡ አዲሱ የካቢኔ አባላት ሹመት ያልጠበቁት መሆኑን የገለጹት አቶ መንገሻ ወንድሙ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው "አዲስ የተሾሙት ሴት ሚኒስትሮች ውጤታማ እንዲሆኑ ሁሉም የድርሻውን ድጋፍ ሊያድርግላቸው ይገባል" ብለዋል። የካቢኔ አባላት ለህብረተሰቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ቀዳሚ ትኩረት በመስጠት በቁርጠኝነት እንዲሰራም ጠይቀዋል፡፡ መምህርት ኢክራም ሐሰን በበኩላቸው ለሴቶች የተሰጠው ልዩ ትኩረት በሌሎች ሴቶች ላይ ልዩ መነቃቃትና ተነሳሽነት የሚፈጥር መሆኑን ነው የገለጹት፡፡ " ሴት ተሻሚዎች ሴቶች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በመፍታት ለትልቅ ደረጃ እንዲበቁና ሀገር እንዲያገለግሉ ማገዝ አለባቸው" ብለዋል፡፡ የማህበራዊ ሳይንስ ሙሁር አቶ ቢንያም ተሰማ በበኩላቸው የሀገር መከላከያ ሚኒስቴርና አዲስ የተቋቋመው የሰላም ሚኒስቴር በሴቶች እንዲመሩ መደረጉ በሀገሪቱ እየተስተዋለ የመጣውን የሥነ-ምግባር ክፍተት ለመድፈን እንደሚያግዝ ጠቁመዋል፡፡ ሴቶች ከቤተሰብ እስከ ማህበረሰብ ለሥነ-ምግባርና ለሰላም መጠበቅ የሚያከናውኗቸው ተግባራት በማንነት ግንባታ ላይ ወሳኝ አሻራ እንደሚያሳርፉም ገልጸዋል። "የሀገሪቱ መከላከያ ሠራዊት አንድነቱን ይበልጥ አጽንቶ ለሀገር ሉአላዊነትና ለሰላም መረጋገጥ ተግቶ እንዲሰራ በአዲስ ሴት አመራር መመራቱ ትክክለኛ ውሳኔ ነው" ሲሉም የማህበራዊ ሳይንስ ምሁሩ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም