ከማህበራዊ ሚዲያዎች አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ስርዓት ያለው አሰራር ለመፍጠር የሚያስችል ህግ እየተዘጋጀ ነው ተባለ

94
አዲስ አበባ ጥቀምት 8/2011 በኢትዮጵያ ከማህበራዊ ሚዲያዎች አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ስርዓት ያለው አሰራር ለመፍጠር የሚያስችል ህግ እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አስታወቁ። የህጉ ዓላማ ሚዲያውን ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨትና ለክፉ ተግባር የሚያውሉ አካላትን ተጠያቂ ማድረግ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ አመልክተዋል። ባለፈው ሳምንት በተከፈተው የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ መክፈቻ ላይ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ ባደረጉትና የመንግስትን የዓመቱ የትኩረት አቅጣጫ በሚያመለክተው ንግግራቸው ዙሪያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ማብራሪያ ሰጥተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምን በተመለከተ ከምክር ቤቱ ለተነሳው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ "የሚዲያ ነጻነት ሲባል በውሸት ስም ገፅ በመከፍት፤ ማንነትን በመደበቅ፣ ያልተገቡ ተግባራትን ማከናወን አይደለም" በማለት አብራርተዋል። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ማንነትን በመደበቂያ በመውሰድና የተለያየ የተጠቃሚ አድራሻ ገፅ በመክፈት ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ እና የውሸት ወሬዎችን  የሚያናፍሱ በርካታ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች መኖራቸውንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል። ''ይህንም በተደራጀ መልኩ ደሞዝ እየተከፈላቸው፤ አንዴ ኦሮሞ ሌላ ጊዜ ደግሞ አማራ፤ አንዱ ቦታ ሴት ፣ ሌላ ቦታ ደግሞ ወንድ ሌላም ሌላም በመሆን የሚሰሩ ስዎችም አሉ" ብለዋል።'' የዚህ ዓይነቱን አፍራሽና አጥፊ ተግባር ለመቆጣጠር በዋናነት ትክክለኛ መረጃዎችን በፍጥነት ማድረስ አንደኛው መፍትሄ ነው ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል። ከዚህ ባለፈ ግን በድብቅ ህዝብን ከህዝብ ለማተራመስ የሚሰሩ አካላትን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ  የሚያስችል ህግ እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል። ህዝቡም በሀሰት ስም ሀሰተኛ የሆኑ የተለያዩ መረጃዎችን በማሰራጨት ጥፋትና ክፋት ከሚሰብኩ አካላት ራሱን በመጠበቅ  ድርጊቱን የመከላከል ትልቁን ድርሻ እንዲወጣ ጠይቀዋል። በኢትዮጵያ ብዙዎቹ የማህበራዊ  ሚዲያ ተጠቃሚዎች ጥቅም በማያስገኝ ተግባር ብዙ ጊዜያቸውን እያባከኑ ነው ሲሉ ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የገለፁት።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም