የተጓተቱ የግንባታ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ በተቀናጀ መልኩ ይሰራል ፤-ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ

69
አዲስ አበባ ጥቅምት 8/2011 መንግስት የተጓተቱ የግንባታ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ በተቀናጀና በታቀደ መልኩ እንደሚሰራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአገሪቱ ርዕሰ ብሄር ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በህዝብ ተወካዮችና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ የመክፈቻ ስነስርዓት ላይ ባቀረቡት ንግግር የምክር ቤቱ አባላት ላነሱት ጥያቄ ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በኢትዮጵያ የግንባታ ፕሮጀክቶችን መጀመር እንጂ የመጨረስ አቅም ደካማ በመሆኑ ምክንያት መንግስትና ህብረተሰቡ ፕሮጀክቶች በጊዜ ተጠናቀው የሚፈለገውን ጥቅም እያገኙ አለመሆኑን ጠቅሰዋል። ይሄንን ችግር ለመቅረፍ መንግስት የግንባታ ፕሮጀክቶችን በታቀደና በተደራጀ መልኩ ለመስራት ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ ገልጸዋል። በመንገድ ግንባታ ላይ ያለውን ዝቅተኛ አፈጻጸም ለማሳደግም ጥረት እየተደረገ መሆኑንና በተያዘው በጀት ዓመት ለዘርፉ 38 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር መበጀቱን አስታውሰዋል። አሁን ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች እስኪያልቁ ሌላ አዲስ ፕሮጀክት እንደማይጀመር ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የትኩረት አቅጣጫው ያላለቁት ላይ ርብርብ ተደርጎ ስራቸውን እንዲጠናቀቁ ማድረግ እንደሆነ አመልክተዋል። በግሉ ዘርፍ ያሉም የግንባታ ፕሮጀክቶች በፍጥነት ተጠናቀው ወደ ስራ እንዲገቡም ድጋፍ እንደሚደረግ ነው ዶክተር አብይ ያስረዱት። በአሁኑ ሰአት በመንግስትና በግሉ ዘርፍ እየተከናወኑ ያሉ የግንባታ ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁ በቅንጅት መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል። ለኤሌክትሪክ ሃይልና አገልግሎት 130 ቢሊዮን ብር በሁለቱ የኤሌክትሪክ ሃይልና አገልግሎት ተቋማት ቦርድ ጸድቆ ስራ ላይ እንደሚውል ገልጸዋል። በኢትዮጵያ ያለውን የሃይል ፍላጎት ለመሙላት የግሉ ዘርፍ ሃይል የማመንጨት ስራ ላይ እንዲሳተፍ በር መከፈቱንና ይህም ትልቅ የሚባል የኢኮኖሚ ማሻሻያ እንደሆነ ጠቅሰዋል። ከአፍሪካ ልማት ባንክና ከሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ጋር በተደረገ ውይይትም ተቋማቱ በፀሐይ ሃይል ዘርፍ እንዲሰማሩ ጥሪ መደረጉንም ገልጸዋል። ሴቶች የኢትዮጵያ ግማሽ አካል ብቻ ሳይሆኑ አብዛኛው የስራ ድርሻ በነሱ ላይ በመሆኑ ከፍተኛ ጫና እንዳለባቸውና ሴቶችን በኢኮኖሚው ተጠቃሚ የማድረግ ጉዳይ የውለታ ሳይሆን ኢትዮጵያን የማጠናከር አላማ እንደሆነ ግንዛቤ ውስጥ መግባት እንዳለበት ገልጸዋል። በደሃ ተኮር የልማት ስራዎች ሴቶችን የልማት ተጠቃሚ የማድረግ ስራ በስፋት እንደሚሰራና ወደ ፊት በሚፈጠሩ አማራጭ የስራ እድሎችም ሴቶችን ተጠቃሚ  የማድረግ ስራ እንደሚሰራም ጠቅሰዋል። መንግስት ሴቶችን በኢኮኖሚውና በአመራርነት ሚና ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ለማጠንከር የጀመረውን ስራ ወደፊትም አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ዶክተር አብይ ተናግረዋል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም