እየተካሄደ ያለውን ለውጥ ማጠናከር እንዲቻል የሚዲያ ተቋማትን መደገፍ ይገባል - ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ

78
አዲስ አበባ ጥቅምት 8/2011 በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ በማጠናከር ሂደት ትልቅ ሚና ሊጫወቱ የሚችሉትን የሚዲያ ተቋማት መደገፍ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩ ይህንን ያሉት በአገሪቱ ሚዲያዎች አጠቃቀምና አሰራር ላይ ያሉትን ችግሮች በተመለከተ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሳ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ላይ ነው፡፡ በዚሁ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት በአገሪቱ ያሉ የግልም ሆነ የመንግስት ሚዲያዎች ከአሰራር ጋር የተያየዘ ሙያዊ የዲስፕሊን ችግሮች አሉባቸው። በዚያው መጠንም በሥራቸው የሚመሰገኑ የሚዲያ ሰዎች መኖራቸውንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል። ለውጡ እንዳይቀለበስ ሚዲያዎች ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው ያሉት ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ ለውጡ ስኬታማ ይሆን ዘንድ መገናኛ ብዙሃን ተግባራቸውን በኃላፊነት እንዲወጡ አሳስበዋል። በዚህ ረገድ በአሁኑ ወቅት የተጀመረው የሚዲያ ነጻነትን የማስፋት ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ዶክተር አብይ ተናግረዋል፡፡ "ሚዲያው የሚያጠፋውን ጥፋት ብቻ ከማየት ባለፈ እያስተማሩ እና እያሰለጠኑ መሄድም ያሻል" ብለዋል፡፡ በተለይም "የግል ሚዲያዎች በቂ የፋይናንስ ምንጭ ስለሌላቸው ጥቂት ግለሰቦች ኪስ እንዳይገቡ መታገዝ አለባቸው" ሲሉ አሳስበዋል። የግሉ ሚዲያ ያሉበትን ችግሮች መፍታት ከተቻለ እውነተኛ ዲሞክራሲ ይረጋገጣል ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ በመሆኑም ሚዲያዎቹን ማብቃትና መደገፍ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ ለዚህም ማስታወቂያ የሚያሰሩ ባለኃብቶች እድሉን ለግሉ ሚዲያችም ጭምር እንዲሰጡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጠይቀዋል። ሚዲያዎችም በመርህ፣ በሚዛናዊነትና ገለልተኛ ሆነው በመስራት ፍርድን ለህዝብ የመተው ሙያዊ ግዴታቸውን ማክበር እንዳለባቸውም አሳስበዋል። "የሚዲያ ሰዎች የአክቲቪዝም ተግባርንና የጋዜጠኝነትን ሙያን መለየት አለባቸው" ሲሉም መክረዋል። "አክቲቪዝቶች እንደ አገር ነቃሽ፣ ተቺ በመሆናቸው ያስፈልጉናል" ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ ጋዜጠኞች ግን በመርህ ኃላፊነትን የሚሸከሙ መሆን አለባቸው ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የሚያስፈልጋት ሚዲያ የመንግስትን እቅድና ተግባራት እየተከታተለ የሚቆጣጠር፣ አቅጣጫ የሚያመላክትና የሚያስተምር ነው ሲሉም ጠቅላይ ሚንስትሩ ገልፀዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም