ከ1972 በኋላ በኢትዮ-ሱዳን ድንበር ጉዳይ የተፈረመ የስምምነት ሰነድ የለም- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ

74
አዲስ አበባ ጥቅምት 8/2011 ኢትዮጵያና ሱዳን ድንበርን በሚመለከት ከ1972 (እአአ) በኋላ የተፈራረሙት የስምምነት ሰነድ አለመኖሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ። የሁለቱን አገሮች ድንበር በሚመለከት ከተጠቀሰው ሰነድ ውጭ የሚቀርብ የስምምነት ፊርማ ተቀባይነት እንደሌለውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨምረው ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአገሪቱ ርዕሰ ብሄር ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በህዝብ ተወካዮችና ፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ የመክፈቻ ስነስርዓት ላይ ባቀረቡት ንግግር የምክር ቤቱ አባላት ላነሱት ጥያቄ ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተዋል። በፕሬዚዳንቱ የመክፈቻ ንግግር የቀረበውን የድጋፍ ሞሽን ምክር ቤቱ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያና ሱዳን ረዥም ዓመታትን የተሻገረ ወዳጅነት ያላቸው አገሮች ናቸው። ኢትዮጵያና ሱዳን ብሎም በሌሎች በርካታ የአፍሪካ አገሮች መካከል የተሰመረው ድንበር በቅኝ ገዥዎች የተሰራ 'አርቴፊሻል' ወሰን መሆኑንም ገልጸዋል። ከሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር ሃሰን አል በሽር ጋር በጉዳዩ ዙሪያ በተደጋጋሚ እንደተነጋገሩ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ "በሁለቱ ወገን ያሉ አርሶ አደሮች ተረጋግተው እንዲኖሩ ሁለቱም አገሮች ወታደሮቻቸውን ከድንበር አካባቢ ለማራቅ ተስማምተዋል" ብለዋል። የጋራ ኮሚሽን ተዋቅሮ ችግሩ እስኪፈታ ዜጎች ሳይፈናቀሉ ባሉበት እንዲቆዩ ስምምነት ላይ መደረሱንም ተናግረዋል። ''ኢትዮጵያና ሱዳን ድንበርን በሚመለከት ተወያይተው የተፈራረሙት በ1972 ዓ.ም ነው'' ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የሁለቱን አገሮች ድንበር በሚመለከት ከተጠቀሰው ሰነድ ውጭ የሚቀርብ የስምምነት ፊርማ ተቀባይነት እንደሌለው ተናግረዋል። "በአህጉረ አፍሪካ የአገሮች ድንበር ጉዳይ አንገብጋቢ በመሆኑ የኢፌዴሪ መንግስት ችግሩን በጥንቃቄ ለመፍታት ይሰራል" ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ ማብራሪያ ሰጥተዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም