የአገሪቱን ሠላም የማስጠበቅና የህግ የበላይነት የማስከበር ተግባር ከአዲሶቹ የካቢኔ አባላት ይጠበቃል

49
አዲስ አበባ ጥቅምት 7/2011 አዲሶቹ የካቢኔ አባላት የአገሪቱን ሠላም በዘላቂነት በማስጠበቅ፣ የህግ የበላይነት በማስከበርና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት  ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ አስተያየት የሰጡ ወጣቶች ጠየቁ። የሚኒስትሮች ምክር ቤት መስከረም 29 ቀን 2010 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ የካቢኔ አባላት ቁጥር ከ28 ወደ 20 ዝቅ እንዲል ውሳኔ ማስተላለፉ ይታወቃል። ይህን ተከትሎ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ወጣቶች አዲስ የተሾሙት የካቢኔ አባላት በየተሰማሩበት የስራ መስክ በአገር ጉዳይ በሃላፊነት ስሜት መስራት እንደሚጠበቅባቸው ነው የተናገሩት። በተለይም የአገሪቱን ሰላም በዘላቂነት በማስጠበቅና የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ በማድረግ ረገድ ጉልህ ድርሻ ሊያበረክቱ ይገባልም ብለዋል። በወጣቶች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችን በመመለስና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት ረገድም ብዙ ስራ እንደሚጠበቅባቸው አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል። አስተያየቱን ለኢዜአ ከሰጡት  መካከል ወጣት ንጉሱ ደሳለኝ እንዳሉት "አዲስ የተመረጡ የካቢኔ አባላት ከዚህ በፊት የነበሩትን ደካማ እና ጠንካራ ጎኖች ያውቁታል፤ ስለዚህ  የነበሩት ስህተቶች አስወግደው በአዲስ መልክ የራሳቸውን ሲስተማቲክ ተጠቅመው መስራት አለባቸው፤  አሁን የካቢኔዎቹ  ቅድሚያ ሰላም ላይ ትኩረት አድርገው ከዛም በኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ዘርፍ ላይ እድገቶችን ማስመዝገብ ይችላሉ፤ ስራቸውንም ከዘረኝነትና ከወገንተኝነት የጸዳ አስተሳሰብ ይዘው ቢመሩ ደስ ይለኛል" ብሏል፡፡ "የተሾሙት የካቢኔ አባላት መጀመሪያ ማድረግ ያለባቸው የአገሪቷን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውሶች በማስወገድ  አገሪቷን ወደ ተሻለ የኢኮኖሚ ደረጃ እንድታድግ ንቁ ህዝባዊ ተሳትፎ በማድረግ ያለባቸውን የስራ ሃላፊነት እንዲወጡ ማድረግ አለባቸው"  በማለት የተናገረው ወጣት ዳዊት ይርሱ  ነው፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም